የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን በማስፋት ዜጎች የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን በማስፋት ዜጎች የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2017(ኢዜአ)፦መንግሥት የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን በማስፋቱ ዜጎች የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች እየተጠቀሙ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከጀርመን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች ላይ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ስራ አስፈፃሚ ብርሃኑ ወልዱ እንዳሉት፤ መንግሥት በገጠሪቱ የሀገሪቱ አካባቢዎች ፍትሐዊ የማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ስርጭት እንዲኖር እያደረገ ነው፡፡
መንግሥት እንደ ሀገር ያለውን እምቅ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለገጠሩ ማህበረሰብ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ከጀርመን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር የካርበን ልቀትን የሚቀንሱ፤ ዓለም አቀፍ የቤተ ሙከራ ፍተሻዎችን ያለፉ 26 ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች ይፋ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት 15 ዓመታት ከ20 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች መሰራጨታቸውን ገልጸው፤ በ2030 ይህን አሃዝ ወደ 31 ሚሊዬን ለማድረስ ታቅዷል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ማህበረሰቡን ከታዳሽ ሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ ንፁህና ሃይል ቆጣቢ የኢነርጂ፣ የጸሃይ እና የባዮ ጋዝ አነስተኛ ቴክኖሎጂዎች እያበለጸገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጀርመን ተራድኦ ድርጅት ፕሮግራም አስተባባሪ አልሙዳቢር ቢን አናማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የጀመረችውን ሽግግር እንደግፋለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተመጣጣኝ ቀጣይነት ያለው እና ዘመናዊ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ከመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡