የሱዳንን ግጭት ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሱዳንን ግጭት ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ፤መስከረም 14/2017 (ኢዜአ)፦የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እና የአሜሪካ መሪዎች የሱዳንን ግጭት ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰባቸውን ሱዳን ትሪቡን ከዋሽንግተን ዘግቧል።
የሁለቱ አገራት ፕሬዘዳንቶች በሱዳን ጉዳይ ላይ ትናንት ውይይት ማድረጋቸውን ዘገባው ጠቁሟል።
የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ፕሬዘዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ እና የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ከውይይታቸው በኋላ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
መሪዎቹ በመግለጫቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ እደረሰ ባለው መፈናቀል ረሀብና ጭካኔ የተሞላበት ግጭት ቆሞ ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ማለታችውን ዘግቧል።
"ለሱዳን ግጭት ምወታደራዊ መፍትሄ የለም" ያለው መግለጫው ጦርነቱ ባስቸኳይ እንዲቆም፣ ወደ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲመለስ እና በሲቪል የሚመራ አስተዳደር እንዲሸጋገር ጥሪ አቅርቧል።
በዳርፉር እየተባባሰ የመጣው ብጥብጥም እንዳሳሰባቸው መሪዎቹ መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ሁለቱም ወገኖች ግጭት አቁመው ወደ ድርድር የማይመጡና የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ ህግ የማያከብሩ ከሆነ የተለያዩ ማዕቀቦችን ከመጣል ጀምሮ በዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።
ሰላማዊ ዜጎችን በተለይም ሴቶችን፣ ህጻናትን እና አረጋውያንን መጠበቅ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም አዘስገንዝበዋል።
በግጭት መስመሮች የእርዳታ አቅርቦትን ለማመቻቸት ሰብዓዊ ፋታዎች እንዲፈጠሩ የሁለቱ አገራት መሪዎች መጠየቃቸውን ሱዳን ትሪቡን በዘገባው አመልክቷል።