ኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ምርትን በጥራት በማምረት የገበያ ተደራሽነቷን ለማስፋት ትኩረት ሰጥታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ምርትን በጥራት በማምረት የገበያ ተደራሽነቷን ለማስፋት ትኩረት ሰጥታለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት የሆርቲካልቸር ምርትን በጥራት በማምረት በአለም ገበያ ተደራሽነቷን ለማስፋት ትኩረት መስጠቷን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በሆርቲካልቸር ዘርፍ የአበባ ልማት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እጸ ጣዕም፣ ሥራሥር፣ እንሰት፣ ቡና፣ የሻይቅጠልና ቅመማቅመም የሚካተቱ ምርቶች ናቸው።
ከእነዚህ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የምርት መጠንና ጥራትን የመጨመር፣ የገበያ መዳረሻ አገራትን የማስፋፋትና ሌሎች በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አብደላ ነጋሽ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ሰፊ አቅም እንዳላት ዘርዝረዋል።
በተለይም በስራ እድል ፈጠራ፣ በምግብ ዋስትና፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለኢንዱስትሪ ግብአትነትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ አቅም እንዳለው አስረድተዋል።
ይህንን አቅም አሟጦ ለመጠቀም በአሰራር ላይ የነበሩ ክፍተቶችን መፍታት የሚያስችል ብሔራዊ የሆርቲካልቸር እስትራቴጂ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
እንደ መሪ ስራ አስፈጻሚው ገለጻ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ምርትን በጥራት እንዲያመርቱ በእስትራቴጂ ትኩረት ከተሰጠው መካከል ነው።
በተጨማሪ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች በክላስተር እንዲያመርቱ እንዲሁም ከባለሃብቶች ጋር በማቀናጀት እንዲሰሩ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ ነው ያሉት።
ብሔራዊ የሆርቲካልቸር እስትራቴጂውን በመተግበር በ2016 በጀት ዓመት በምርት ጥራት፣ አቅርቦት፣ ጸጥታና ሌሎች ያጋጠሙ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በፍራፍሬ እንዲሁም አትክልትና እጸ-ጣዕም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ጠቁመው፤ ምርትን በጥራትና በብዛት በማምረት በአፍሪካ እንዲሁም በአለም ገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ሳይበላሹ ለውጭ ገበያ ተደራሽ ለማድረግ በቀዝቃዛ ኮንቴነሮች የአገልግሎት ዘርፍ ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ለምርት ጥራት ትኩረት እንዲሰጡ ድጋፍና ክትትል በማድረግ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ያለውን ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን መሪ ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የሆርቲካልቸር ምርት 535 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።