ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም በፀጥታው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም በፀጥታው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልችን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚከናወነውን ስራ ለማጠናከር በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሥር የተቋቋመውን የሬድ ፎክስ ማዕከልን (Red Fox Center) እንዲሁም በፌደራል ፖሊስ እየተገነባ ያለውን የፎረንሲክ ማዕከል በቁሳቁስ፣ አቅም ግንባታና በልምድ ልውውጥ መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።


 

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከዩናይትድ ኪንግደም የብሔራዊ ወንጀል መከላከል ኤጀንሲ (UK National Crime Agency) ጋር ያለው ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ለተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በእንግሊዝ ሀገር ለሰጠው የትምህርት እድል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልች አገራቸው በፀጥታው ዘርፍ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

በቀጣይ ትብብሩን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና በዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የወንጀል መካከከል ኤጀንሲ መካከል የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈረም መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም