ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን አስደናቂ የቱሪዝም ኃብቶች ዓለም እንዲያውቃቸው ከሁላችንም ብዙ ሥራ ይጠበቃል - አስጎብኝዎች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2017 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን አስደናቂ የቱሪዝም ኃብቶች ዓለም እንዲያውቃቸው ከሁላችንም ብዙ ሥራ ይጠበቃል ሲሉ የተለያዩ አስጎብኝ ድርጅቶች ገለጹ።

ከከፍተኛው ሥፍራ ራስ ደጀን እስከ ዝቅተኛው ዳሎል የሚገኙባት የሁሉ መገኛና የ13 ወር ጸጋ ባለቤት ኢትዮጵያ አየሯ ተስማሚ ሕዝቧ እንግዳ ተቀባይና መስተንግዶ አዋቂ መሆኑ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ የሰው ዘርና የቡና መገኛ፣ ጤፍ አምርታ ለዓለም ከማስተዋወቅ ባለፈ በበርካታ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤትነት ትጠቀሳለች።

የረዥም ዘመን የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ባለቤት፣ የፓን-አፍሪካኒዝም መነሻና የቀደምት ሥልጣኔና ሌሎችም ዘርፈ-ብዙ ታሪኮች ባለቤት በመሆን በምሳሌነት ትነሳለች።

በመሆኑም ይህችን ድንቅ ሀገር በዓለም በስፋት በማስተዋወቅ ሁሉም የሚጎበኛት ሀገር ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የያማ ኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬሽን ማኔጀር ትዕግስት ሲሳይ፤ የኢትዮጵያን አስደናቂ የቱሪዝም ኃብቶች ዓለም እንዲያውቃቸው ከሁላችንም ብዙ ሥራ ይጠበቃል ብለዋል። 

የዴኩቭሪር ኢትዮጵያ አስጎብኝ ባለቤት ሰለሞን ጌቱ፤ ኢትዮጵያ ያሏትን ታሪካዊ ቅርሶች፣ ተፈጥሯዊ ኃብቶችና ባህላዊ ትውፊቶች ለዓለም በማስተዋወቅ ወደ ኃብት ማሸጋገር ይገባል ብለዋል፡፡ 


 

የሪሊያንስ አፍሪካ ቱር ኤንድ ትራቭል ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥራች ዑስማን መሀመድ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ኃብት እስካሁን ብዙም ያልተጠቀምንበት ዓይነተኛ የእድገት መሠረት መሆኑን ገልፀዋል።

የእስልምና ኃይማኖት መርሆዎችን መሠረት ያደረገ የሀላል ቱሪዝም አገልግሎት ለሚሹ ቱሪስቶችም አማራጭ የጉብኝት አገልግሎቶችን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።


 

ኢትዮጵያን በዓለም ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ መንግሥት የሰጠውን ትኩረት አድንቀው፤ ለሀገራችን ሁላችንም ባለቤት ሆነን መሥራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም አቅም ለዘመናት ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑን ያነሱት አስጎብኝዎቹ፤ አሁን የተጀመረው የቱሪዝም መሠረተ-ልማት ግንባታና የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ለዚህም ከመንግሥት ጥረት ባሻገር ሁሉም የዘርፉ ተዋንያንና አጠቃላይ ዜጎች በባለቤትነት መሥራት እንዳለባቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያን አስደናቂ የቱሪዝም ኃብቶች ዓለም እንዲያውቃቸው ከሁላችንም ብዙ ሥራ ይጠበቃል በማለትም አጽንዖት ሰጥተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች እየተስፋፋ የመጣውን የግጦሽ ስጋት ዘላቂ እልባት መስጠትም ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም