የሶማሊያ መንግስት ወቅታዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊያን ለሶማሊያ አንድነት የከፈሉትን መስዋዕትነት የካደ ነው - አንጋፋው ዲፕሎማት ጥሩነህ ዜና - ኢዜአ አማርኛ
የሶማሊያ መንግስት ወቅታዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊያን ለሶማሊያ አንድነት የከፈሉትን መስዋዕትነት የካደ ነው - አንጋፋው ዲፕሎማት ጥሩነህ ዜና
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2017(ኢዜአ)፦የሶማሊያ መንግስት ወቅታዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊያን ለሶማሊያ አንድነት የከፈሉትን መስዋዕትነት የካደ ነው ሲሉ አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ተናገሩ።
አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፤ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ህዝቦች በባህልና በቋንቋ የተሳሰረ ማንነት ያላቸው ወዳጅ ህዝቦች መሆናቸውን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
ሶማሊያ ችግር በገጠማት ወቅትም ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሀገር በተለየ መልኩ መስዋዕትነት በመክፈል ለሶማሊያ አንድነት ከፍተኛ ሚና ማበርከቷን ነው የገለጹት፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ የአሸባሪ ቡድኖችን ኃይል ለመግታት ወሳኝ ሚና ማበርከታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችም ለሶማሊያ መልሶ ግንባታ ዓለም አቀፍ በጎ ፈቃድና ድጋፍ እንዲገኝ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ የሚመነጨው የውጭ ፖሊሲዋ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ነገር ግን አሁን ላይ የሶማሊያ መንግስት በቀጣናው ጂኦ ፖለቲካ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ኃይሎችን ጭምር በመጋበዝ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተጻረረ መልኩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያዊያን ለሶማሊያ አንድነት የከፈሉትን መስዋዕትነት የካደና በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚፈጥር መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው እየተፈጠረ ያለውን ችግር በሰላምና ዲፕሎማሲ ለመፍታት እያከናወነች ያለውን ስራም አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በረዥም ዘመን ታሪኳ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ ድል እያስመዘገበች ማለፏን አስታውሰው፤ አሁን ላይም የሚገጥሟትን ፈተናዎች ወደ ድል በመቀየር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፈተናዎች በገጠሟት ቁጥር ጠንክራ የምትወጣ ሀገር ነች ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡