የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በበጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ተኪ ምርቶች ለማምረት ማቀዱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በበጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ተኪ ምርቶች ለማምረት ማቀዱን ገለጸ

አዳማ፤መስከረም 14/2017(ኢዜአ)፡-የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተያዘው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከሚቀርብ በተጨማሪ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ተኪ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝ ገለፀ።
ፓርኩ እቅዱን ለማሳካትና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ይበልጥ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ ለኢዜአ እንደገለፁት በፓርኩ የተገነቡት ሁሉም የማምረቻ ሼዶች በባለሀብቶች ተይዘዋል።
ፓርኩ ውስጥ ከገቡት 13 ኩባንያዎች መካከል 11 የሚሆኑት ወደ ምርት መግባታቸውን ጠቅሰው የተቀሩት ኩባንያዎች በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ወደ ምርት ለማስገባት ርብርብ እያደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም ባለፈው ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ተኪ ምርት በማምረት ለሀገር ውሰጥ ገበያ ማቅረብ መቻሉን አስታውሰው በተመሳሳይ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለሀገሪቱ ማስገኘቱንም እንዲሁ።
በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ለውጭ ገበያ ከሚያቀርበው በተጨማሪ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ተኪ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ውስጥ የራሱን ድርሻ ለመጫወት አቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ነው የገለጹት።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው በፓርኩ ውስጥ ወደ ማምረት የገቡ ባለሃብቶችን ያነቃቃ ከመሆኑም ባለፈ ተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብም ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም የባለድርሻ አካላት ለፓርኩ ውጤታማነት የጎላ ሚና ያላቸው በመሆኑ ኩባንያዎች የማምረት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ገቢንም ለማሳደግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ያለመ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 9 ሺህ ለሚሆኑት ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልጸዋል።
በጥሬ እቃ አቅርቦት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎትና አቅም ግንባታ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ኤጄንሲያቸው ከፓርኩ ጋር ትስስር ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የአዳማ ህብረት ስራ ማስፋፊያ ኤጄንሲ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ዓለሙ ናቸው።
በተለይም የፕላስቲክ፣ የጨርቃጨርቅና የግብርና ምርት ጥሬ እቃዎችን ከማህበራት፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችና ከአርሶ አደሩ ጋር ፓርኩን ቀጥታ በማገናኘት የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት ላይ በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።