የቻይና ባለሀብቶች በቱሪዝም መሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና ባለሀብቶች በቱሪዝም መሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2017(ኢዜአ)፦ የቻይና ባለሀብቶች በቱሪዝም መሰረተ-ልማት ግንባታ፣ በሆቴል፣ በሎጅ እና በቱሪዝም ትምህርት ልማት ዘርፎች እንዲሳተፉ የቱሪዝም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች ከቻይና-ሽያንዥ ከመጡ ባለሀብቶች ጋር በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም የቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት አመራጮች ማብራሪያ አቅርበዋል።
መንግስት በቱሪዝም ኢንቨስትመንት መሳተፍ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ማበረታቻ የመሬት አቅርቦትን ጨምሮ፣ ከቀረጥ ነጻ የሆነ ለስራ የሚውል የግንባታ ግብዓት እንደሚያቀርብ በማብራሪያው ተመላክቷል።
በተጨማሪም በቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሀይልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መዳረሻዎች አማራጭ መብዛት ለቱሪስቶችና በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች መልካም አጋጣሚ መሆኑም ተገልጿል።