ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓል ከኃይማኖታዊ አስተምህሮው ባሻገር የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ መተባበርና አብሮነት የሚገለጽበት ነው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2017(ኢዜአ)፦ የመስቀል ደመራ በዓል ከኃይማኖታዊ አስተምህሮው ባሻገር የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ መተባበርና አብሮነት የሚገለጽበት መሆኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት የአስተዳደር መምሪያ ዋና ኃላፊ መምህር ዶክተር አካለወልድ ተሰማ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ የመስቀል ደመራ በዓል ነው፡፡

ደመራ መጨመር፤ መሰብሰብ የሚል ትርጓሜ ሲኖረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ምዕመናን ደመራ ደምረው ችቦ እያበሩ በዓሉን በሃይማኖታዊ ስርዓት ያከብራሉ፡፡  

በዓሉ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ አብሮነት፣ የምስጋናና የተስፋ እሴቶች የሚገለጹበት ኃይማኖታዊ ክብረ-በዓል ሲሆን፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።   


 

የበዓሉ አከባበርም በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርት እና ባህል ተቋም በዓለም በማይዳሰስ ተመዝግቧል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት የአስተዳደር መምሪያ ዋና ኃላፊ መምህር አካለወልድ ተሰማ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የመስቀል ደመራ በዓል የአንድነትና አብሮነት እሴትን የሚያጠናክር ነው፡፡

መስቀል ደመራ በኃይማኖታዊ አስተምህሮው ባሻገር ስለ ሰላም፣ አንድነትና ህብረት በተግባር የሚገለጽበት ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ 


 

መንፈሳዊ በዓላት ከኃይማኖታዊ አስተምህሮ ባሻገር ለህዝቦች አንድነትና አብሮነት መጎልበት ትልቅ  ሚና እንዳላቸውም ነው ያነሱት፡፡

ከዚህ አኳያ ከመስቀል ደመራ በዓል አንድ መሆንን፣ መተባበርን እና ህብረትን የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የበዓሉ አከባበር በርካታ ጎብኚዎችን ወደ ሀገር የሚሰብ መሆኑን ጠቁመው ለቱሪዝሙ ዕድገትም የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡


 

አብሮነትና መተባበር የሀገር ግንባታ መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ በበዓላት ጊዜ የሚታየው እርስ በርስ መተጋገዝና አንድነት የሰርክ ተግባር ሆኖ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በዓሉ እንደከዚህ ቀደሙ ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም