በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ 102 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ የአስፋልት መንገዶች ጥገና ለማከናወን እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ 102 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ የአስፋልት መንገዶች ጥገና ለማከናወን እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2017 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2017 በጀት ዓመት 102 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ የአስፋልት መንገዶችን ጥገና ለማከናወን እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በተያዘው በጀት ዓመት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የጀመረውን የአስፋልት መንገድ ጥገና ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።
በክረምቱ ከባድ ዝናብ ምክንያትና በመንገድ ሀብት አጠቃቀም ጉድለት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን መንገዶች በመለየት የጥገና ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም አመልክቷል።
የአስፋልት መንገድ ጥገና ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል ከጎፋ መብራት ኃይል በቀይ መስቀል ወደ አደይ አበባ የሚያደርሰው መንገድ እንደሚገኝበት ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ከጀርመን አደባባይ ወደ ለቡ መብራት ኃይል፣ ከሲኤምሲ የተባበሩት ነዳጅ ማደያ ወደ ሰሚት ፔፕሲ ፋብሪካ፣ አየር ጤና አደባባይ፣ ጎፋ መብራት ኃይልና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ የጥገና ስራዎች መከናወናቸውን ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በበጀት ዓመቱ 102 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ የአስፋልት መንገድ ጥገና ለማከናወን እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።