ቀጥታ፡

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የክልሉ ወጣቶች በ”አምስት ሚሊዮን ኮደርስ" ስልጠና ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2017(ኢዜአ):- የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የክልሉ ወጣቶች እየተሰጠ በሚገኘው በ''አምስት ሚሊየን ኮደርስ’’ የስልጠና መርሃ ግብር ላይ እንዲሳተፋ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በይፋ የተጀመረው የ''አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ መርሃ ግብር ፕሮጀክት "ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ወጣቶች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ ለማድረግ እየተተገበረ ይገኛል።

የኢትዮ-ኮደርስ ፕሮግራም መንግስት ወጣቶችን ለማብቃት፣ ፈጠራን ለማጎልበትና የዲጂታል ዘመንን ግዙፍ አቅም ለመጠቀም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በክልሉ ስልጠናውን የሚያስተባብር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንም ገልጸዋል።

ሥልጠናው ወጣቶቹን የክህሎት ባለቤት ከማድረግ ባለፈ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጎች እንዲሆኑ ያግዛል ነው ያሉት።

የክልሉ ወጣቶችም ዘመኑ የሚፈልገው ብቁ ዜጋ መሆን የሚያስችላቸውን ይህን ሥልጠና በመውሰድ ራሳቸውን ብቁና ተወዳዳሪ እንዲያደርጉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም