ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የትብብር ስምምነቶቻቸውን ለመተግበር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2017 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የተፈራረሟቸውን የተለያዩ የትብብር ስምምነቶች ተፈጻሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ መንደይ ሴማያ ኩምባ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ላይም አምባሳደር ነቢል የኢትዮጵያ መንግስት ለደቡብ ሱዳን መንግስትና ሕዝብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት የጋራ ፍላጎታቸውን መሰረት በማድረግ በመሰረተ ልማትና አቅም ግንባታ የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ወደ ትግበራ ማስገባት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ መንደይ ሴማያ ኩምባ የኢትዮጵያ መንግስት ለደቡብ ሱዳን የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን የመተግበር ሂደት ውስጥ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በማድነቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


 

የደቡብ ሱዳን መንግስት የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ለመተግበር ቁርጠኛ ነውም ብለዋል።

አገራቸው በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም በዩጋንዳ ካምፓላ በሚካሄደው የናይል ቤዚን ስብስባ ውጤታማ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀቷንም አመልክተዋል።

ሁለቱ ወገኖች የዜጎችን እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የሚረዳ ከቪዛ ነጻ ስምምነት መፈራረም አስፈላጊነት ላይ መወያየታቸውን ደቡብ ሱዳን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም