የዓለም ፋይናንስ አሰራር ጥልቅ ማሻሻያ ያስፈልገዋል - አንቶኒዮ ጉተሬዝ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2017 (ኢዜአ):- የዓለም ፋይናንስ አሰራር ጥልቀት ያለው ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ነባራዊውን ዓለም የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት ብለዋል።

ከ79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢኒሼቲቭ የሆነው የመጪው ጊዜ ጉባዔ (Summit of the Future) በኒውዮርክ እየተካሄደ ይገኛል።

የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ አሰራር የእይታ ለውጥ ማምጣት፣ የተገቡ ቃልኪዳኖችን መፈጸምና የረጅም ጊዜ ችግሮችን መፍታት ላይ የጉባዔው ዋንኛ ማጠንጠኛ ጉዳዮች ናቸው።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጉባኤው ላይ የተሰበሰብነው የባለብዝሃ ወገን ስርዓትን ከተጋረጠበት የሕልውና አደጋ ለመታደግ ነው ብለዋል።

ጉባኤው ዓለም አቀፍ ተቋማት የተመድ ቻርተር እሴቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ይበልጥ ሕጋዊ፣ ፍትሐዊና ውጤታማ መሆን የሚያስችላቸው ጥልቅ ማሻሻያዎች በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ሀሳቦችን እንዲያነሳ ጠይቀዋል።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈተናዎች የ21 ክፍለ ዘመንን መፍትሔዎች ይሻሉ ያሉት ዋና ፀሐፊው ሁሉን አሳታፊና ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጡ ማዕቀፎች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል።


 

በበርካታ ውስብስብና አሳሳቢ ፈተናዎችና ስጋቶች እያለፈች የምትገኘው ዓለም የገጠሟት ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች በዘላቂ ልማት ላይ አሉታዊ ተጽእኖዎችን ማሳደሩን ነው የገለጹት።

ይህም በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት እድገት ላይ ጋሬጣ እንደሆነ ተናግረው ይህ ፍትሐዊ ካልሆነው የፋይናንስ አቅርቦት ጋር ተዳምሮ ተደራራቢ ጫናዎችን መፍጠሩን አመልክተዋል።

በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረጋው የዓለም የፋይናንስ ስርዓት የአገራቱን የዘላቂ ልማት ትልሞችና ፈተናዎች ባማከለና ከወቅቱን የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ ጥልቅ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፋይናንስ ስርዓቱን ለመለወጥ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ስራዎች ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም ሁለን አሳታፊና አካታች ያደረገ ፍትሐዊ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ገልጸው የአፍሪካ፣ እስያ፣ ፓሲፊክና ላቲን አሜሪካ በምክር ቤቱ ውክልና ሊያገኙ ይገባል ነው ያሉት።

ዓለም አቀፍ የትብብር መድረክን ፍትሃዊ፣ አሳታፊና ትስስርን አጎልባች እንዲሆን ቁርጠኝነት የተሞላባቸውን እርምጃዎች መውሰድ እንደሚያስፈልግ አክለዋል።

ትናንት በመጪው ዘመን ጉባዔ መክፈቻ ቀን አገራት ዓለም አቀፍ የዲጂታል ማዕቀፍና የቀጣይ ትውልድ የመርሆዎች መግለጫን ያካተተ ታሪካዊ የተባለለት ‘Pact for the future’ (የቀጣይ ዘመን ስምምነት) ማጽደቃቸው የሚታወስ ነው።

ጉባዔው የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ማምሻውን ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም