ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች መስተጋብር በትክክል መለየት የሚያስችል አትላስ ሊያዘጋጅ ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 13/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ቋንቋዎች መስተጋብር እና ምንነት በትክክል መለየት የሚያስችል የቋንቋዎች መግለጫ አትላስ ለማዘጋጀት በሂደት ላይ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር ዮሐንስ አድገህ (ዶ/ር)፤የሰው ልጆችን ተግባቦት በመፍጠር የእለት ከዕለት እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ቋንቋ ማይተካ ሚና እንዳለው ይታመናል።

ኢትዮጵያም በዓለም ላይ ብዝኅ ቋንቋ ከሚነገርባቸው ሀገራት መካከል አንዷ በመሆን የብዝኅ ቋንቋና ባህል ባለቤት የሆኑ ዜጎች የሚኖሩባት የኅብር ምድር መሆኗም ይታወቃል።

በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች መስተጋብር በትክክል መለየት የሚያስችል አትላስ ሊያዘጋጅ መሆኑ ታውቋል።

በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር ዮሐንስ አድገህ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያዊያን ባህልና ቋንቋ መካከል ያለውን ትስስር፣ምንነትና ዝምድና የሚያስረዳ መረጃ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የቋንቋ መግለጫ አትላስ ማዘጋጀት ለቋንቋና ባህል ልማት የዜጎችን የእርስ በእርስ ትስስር በማጠናከር ጸጋዎቻቸውን በተሻለ ግንኙነት መጠቀም የሚያስችል ተግባቦትን የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የሚነገሩ ልሳነ ብዙ ቋንቋዎች የያዟቸው ሀገር በቀል ዕውቀት፣ልማድ፣ለዛና ቀለማትም ሀገርን ከቱሪዝም ልማት ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በብዝኅነት የሚነገሩ ቋንቋና የሚኖሩ ባህሎችንም በሚገባ በመሰነድ ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚም የኢትዮጵዊያንን ቋንቋዎችን ያደጉ፣ በማደግ ላይ ያሉ፣ ድንበር ተሻጋሪ፣ በመጥፋት ላይ ያሉ እና ጥንታዊ ድርሳናት በሚሉት ፈርጆች ላይ ጥናት ማካሄዱን አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የጽንሰ ሃሳብ፣ቃላትና ስያሜ እንዲኖራቸው ለማድረግ ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ጽሕፈት፣ መዝገበ ቃላትና ሰዋሰው የማዘጋጀት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

በመሆኑም ለቋኝቋዎች አትላስ መግለጫና ፕሮፋይል ዝግጅት ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመነጋገር ለመስራት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የቋንቋ ብዝኃነት የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ መሆኑን የሕንድ፣ ናይጄሪያና ቻይና ተሞክሮዎች ጥሩ ማሳያዎች መሆናቸው ይነገራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም