የጎቤ እና ሺኖዬ ፌስቲቫል የኦሮሞን ህዝብ ባህልና እሴት በማስተዋወቅ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ መልካም ዕድል የፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎቤ እና ሺኖዬ ፌስቲቫል የኦሮሞን ህዝብ ባህልና እሴት በማስተዋወቅ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ መልካም ዕድል የፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 13/2017(ኢዜአ)፦የጎቤ እና ሺኖዬ ፌስቲቫል የኦሮሞን ህዝብ ባህልና እሴት በማስተዋወቅ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ መልካም ዕድል የፈጠረ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ ሲከናወን የቆየው ስድስተኛ የጎቤ እና የሺኖዬ የወጣቶች ባህላዊ ጭፈራ ፌሲቲቫል የማጠቃለያ ስነ-ስርዓት ከአድዋ ድል መታሰቢያ እስከ ኦሮሞ ባህል ማዕከል በተደረገ የጎዳና ላይ ትርኢት ተከናውኗል።
በመርሃ ግብሩ ላይ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ በዚሁ ወቅት፤ ፌስቲቫሉ ላለፉት 13 ቀናት በአዲስ አበባና በሸገር ከተማ አስተዳደር ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ወጣቶችና ልጃገረዶች በተለያዩ ባህላዊ አልባሳት አጊጠው ፌስቲቫሉን ማድመቃቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ፌስቲቫሉ አብሮነትና አንድነት ይበልጥ በሚያገለብት መልኩ መከናወኑን አንስተው፤ የኦሮሞን ህዝብ ባህልና እሴት በማስተዋወቅ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ መልካም ዕድል የፈጠረ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ የሚከበሩት የደመራ፣ የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት ወጣቶች ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲያከብሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ሻምበል አዱኛና አስቴር አለሙ ፌስቲቫሉ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ መከበሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡
ጎቤ እና ሺኖዬ የክረምቱን ወራት መጠናቀቅ ብሎም የአዲስ ዓመት ተስፋን የሚያንጸባርቁ መገለጫዎች መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ፌስቲቫሉ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡