በቀጣዮቹ አስር ቀናት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2017(ኢዜአ):-በቀጣዮቹ አስር ቀናት በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያ እንደሚያመለክተው በቀጣዮቹ አስር ቀናት በሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እንዲሁም በመካከለኛ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል።

በምዕራባዊ አጋማሽና ወደ ደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች የዝናብ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ሥፍራዎችም በሁለተኛው የዝናብ ወቅታቸው ዝናብ ማግኘት ይጀምራሉ።

በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑንም ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያመለክታል።

የዝናቡ ሁኔታ ለግብርና ሥራ ምቹ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚፈጥርና ቀደም ብሎ ለተዘሩት፣ ፍሬ በማፍራት ላይ ለሚገኙና ዘግይተው ለሚዘሩ ሰብሎችና ቋሚ ተክሎችም ጠቃሚ መሆኑ ተመላክቷል።

በባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊዜ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ በላይኛውና መካከለኛ አዋሽ፣ ዋቤ ሸበሌ እና ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ላይ እስከ ከፍተኛ እርጥበት የሚኖር መሆኑም ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል በክረምት ወራት ከተገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት ጋር ተያይዞ የውሃ መጠናቸው የጨመረባቸው ተንዳሆ፣ ከሰም፣ ቆቃ፣ ርብ፣ ጣናበለስ እና ፊንጫኣ ግድቦች በሚገኙባቸው የታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎች ከመጠን በላይ የግድብ መሙላት ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

የሰሜንና ሰሜን ምስራቅ የዝናብ ስርጭት በመጪዎቹ አስር ቀናት እየቀነሰ ሊሄድ እንደሚችል ነው የተተነበየው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም