በሲዳማ ክልል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በታችኞቹ የትምህርት ደረጃዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በታችኞቹ የትምህርት ደረጃዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው
ሀዋሳ፤መስከረም 13/2017 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በታችኞቹ የትምህርት ደረጃዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የ2017 ዓመት የመማር ማስተማር ሥራ ዛሬ ተጀምሯል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዘገየ ኩይሳ የዓመቱን ትምህርት ሲያስጀምሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልና በዘርፉ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን በታችኞች የክፍል ደረጃዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከለ የመማሪያ ክፍሎች ደረጃን የማሻሻል፣ የመምህራንን አቅም የማሳደግና ግብአት የማሟላት ሥራዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ህዝብን በማሳተፍ በተከናወኑ በእነዚህና መሰል ሥራዎች በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻል መታየት መጀመሩንም ጠቁመዋል።
በተያዘው የትምህርት ዘመንም በክልሉ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱንም አቶ ዘገየ ገልጸዋል።
ለመማር ማስተማር ሥራው ከ1 ሺህ 300 በላይ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
በክልሉ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ከ2013 ጀምሮ ባለሃብቱንና ህዝብን በማስተባበር የተገነቡትን ጨምሮ ከ1ሺህ 352 በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ዘንድሮ በአዲስ ምዕራፍ ሥራ እንደሚጀመሩም ነው ያስታወቁት።
በዚህም የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በታችኞቹ የትምህርት ደረጃዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በተለይ በ6ኛ፣ በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ግብ ተጥሎ የዓመቱ ትምህርት መጀመሩንም አቶ ዘገየ ተናግረዋል።
"የትምህርት ዘመኑን ስኬታማ ለማድረግ ከባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት የሚሰራው ሥራ በቀጣይም ይጠናከራል" ብለዋል።
የሀዋሳ ከተማ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ ብርሃኑ ደሳለኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዓመቱ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ክፍተትና ጥንካሬን የገመገመ የንቅናቄ መድረክ መካሄዱን ጠቅሰዋል።
የመማሪያ ክፍሎችን ለትምህርት ዝግጁ ማድረግን ጨምሮ በተማሪዎች ውጤትና ሥነምግባር ላይ መምህራን ተወያይተው የዓመቱ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩንም ተናግሯል።
የትምህርት ሥራ በጊዜ የተገደበ በመሆኑ ከመጀመሪያ ጀምሮ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲማሩ አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግ አመልከተዋል።
በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ ትቅደም የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ልንገርህ ቢያድግልኝ፣ በክረምት ወራት የመማሪያ ክፍሎችንና የትምህርት ቤቱን ግቢ የማስዋብ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ተማሪዎችን በወቅቱ ከመመዝገብ ጀምሮ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ዛሬ ትምህርት መጀመሩንም ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የስድስተኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛው ውጤት አምጥታ ማለፏን የተናገረችው ተማሪ ኑሃሚን ወንዱ በበኩሏ፣ የመምህራኖቿ ድጋፍና የራሷ ጥንካሬ ለተሻለ ውጤት እንዳበቃት ተናግራለች።
ዘንድሮም በትምህርት ቤቱ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምና ተግታ በማጥናት ውጤታማ ለመሆን ማቀዷን ገልጻለች።
በሲዳማ ክልል ባሉ የተለያዩ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ዛሬ የትምህርት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር መከናወኑ ታውቋል።