ስድስተኛው ዙር ''ጎቤና ሺኖዬ'' የወጣቶች የባህላዊ ጭፈራ ፌስቲቫል ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
ስድስተኛው ዙር ''ጎቤና ሺኖዬ'' የወጣቶች የባህላዊ ጭፈራ ፌስቲቫል ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2017(ኢዜአ):-በአዲስ አበባና በሸገር ከተማ ሲካሄድ የቆየው ስድስተኛ ዙር ''ጎቤና ሺኖዬ'' የወጣቶች የባህላዊ ጭፈራ ፌስቲቫል ተጠናቀቀ።
በኦሮሞ ባህል ማዕከል በተካሄደ የመዝጊያ መርሀ-ግብር ላይ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ፣ አባገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎችና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጎቤና ሺኖዬ'' ወጣት ወንዶችና ሴቶች ክረምቱ አልፎ የ'ብራ' ወቅት መምጣቱን ለማመላከት በባህላዊ አልባሳት አጊጠው የሚጨፍሩት ባህላዊ ጭፈራ ነው።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ የ''ጎቤና ሺኖዬ'' አዲስ አመትን የባህላዊ ጭፈራ ፌስቲቫል ከጳጉሜ 1 ቀን 2016 ጀምሮ ሲከናወን አንደነበር አስታውሰዋል።
በፌስቲቫሉ ወጣት ወንዶችና ሴቶች የተለያዩ ባህላዊ አልባሳት አጊጠው ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ሲያከብሩት ነበር ብለዋል።
ፌስቲቫሉ ወጣቶች አንድነታቸውን ያጠናከሩበት፣ ደስታቸውን ያጋሩበትና ተስፋቸውን ያንጸባረቁበት እንደነበርም ነው የተናገሩት።
ወጣቶቹ ከጳጉሜ ጀምሮ በተለያዩ ጎዳናዎች፣ በታዋቂ ግለሰቦችና በመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች መኖሪያ ቤት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት ሲገልጹና የተለያዩ ስጦታዎችን ሲቀበሉ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባና በሸገር ከተማ አስተዳደር ሲካሄድ የቆየው የጎቤና ሽኖዬ ጨዋታ፤በአባቶች ምርቃት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በቀጣይ የሚከበሩት የዳመራ፣ የመስቀል እና የእሬቻ በዓላት ወጣቶች ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲያከበሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።