ቀጥታ፡

በቅርብ ዓመታት የተገነቡ የቱሪዝም መስህቦች የዘርፉ የጥራትና ስኬት ማሳያዎች ናቸው - አስጎብኚዎች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2017(ኢዜአ):- በቅርብ ዓመታት የተገነቡ የቱሪዝም መስህቦችና መዳረሻ ስፍራዎች የዘርፉ የጥራትና ስኬት ማሳያዎች መሆናቸውን የተለያዩ አስጎብኚ ድርጅቶች ገለጹ።

ኢትዮጵያ እንደ ታሪክ ማህደርነቷ በጸጋዋ ልክ መልማት ተስኗት ለዓመታት ከነበረችበት ሰመመን በመንቃት የቱሪዝም ሀብቷን ጥቅም ላይ ማዋል ጀምራለች።

ቱሪዝም መንግሥት ካስቀመጣቸው አምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ ዘርፉን የሚያሳልጡ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ይገኛል።

አስጎብኚዎች የጉዞ ፓኬጆችን በማዘጋጀት ለጎብኚዎች የሚሆኑ የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋትና በጥራት በመገንባት ላይ ናቸው።

የሪሊያንስ አፍሪካ ቱር ኤንድ ትራቭል ሰርቪስ መሥራች ዑስማን መሀመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ሁኔታና ምቹ መስተንግዶ ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም አላቸው።

እነዚህ እምቅ የቱሪዝም ሃብቶች የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የኢኮኖሚ መሰረት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባና በክልሎች የሚገነባቸው የቱሪዝም ሀብቶች ኢትዮጵያ ያላትን አሳምራና አስውባ ጥቅም ላይ እንድታውል እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።


 

የዴኩቭሪር ኢትዮጵያ አስጎብኚ ባለቤት ሰለሞን ጌቱ፤ በጎርጎራ፣ ወንጪ፣ በአዲስ አበባና ሌሎችም አካባቢዎች የተገነቡ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ለሀገር ሃብትና ለበርካቶች የስራ እድል የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።

በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ አልሚዎች በምን አይነት የጥራት ደረጃ መሥራት እንዳለባቸው በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።


 

የያማ ኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬሽን ማናጀር ትዕግስት ሲሳይ፤ ባለፉት ዓመታት አዳዲስ የቱሪዝም ሀብቶች መልማታቸውንና ነባሮችም እንድሳት እንደተደረገላቸው አመልክተዋል።

የቱሪዝም ልማቱ አስጎብኚ ድርጅቶችን ያነቃቃና የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም