ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጠ መልኩ እንዲከናወን ጠየቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጠ መልኩ እንዲከናወን ጠየቀች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2017(ኢዜአ):- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጠ መልኩ እንዲከናወን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ጠየቁ።
በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 79ኛው የ.ተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባዔ የዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢኒሼቲቭ የሆነውና ከ140 በላይ የሀገር መሪዎች የሚሳተፉበት የመጪው ጊዜ ጉባዔ(Summit of the Future) ተከፍቷል።
በዚሁ ጉባዔ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ እየተሣተፈ ይገኛል።
በጉባዔው ላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጠ መልኩ እንዲከናወን ጠይቀዋል።
አምባሳደር ታዬ ምክር ቤቱን ለማሻሻል የሚደረገው እንቅስቃሴ የአፍሪካን የውክልና አድማስ ከሁሉም መመዘኛዎች አንጻር ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባውም አመላክተዋል።
ስምምነቱ ሁሉንም ሀገራት በእኩል አይን የሚመለከተው ጊዜ አይሽሬ የሆነው የተመድ መመሥረቻ ቻርተር ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ለማድረግ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በመጪው ጊዜ ጉባዔ ላይ የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ሥርዓትን ሪፎርም ለማድረግ በትውልድ የአንድ ጊዜ ዕድል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ጉባዔ ሠነድ ከ143 ሀገራት በላይ ድጋፍ በማግኘት ፀድቋል።
አምባሳደር ታዬ ስምምነቱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ሚኒስትሩ ሀገራት ድህነትን ለማጥፋት የሚያደርጉት ጥረት በራሳቸው የፖሊሲ ማዕቀፍ ምርጫ አግባብ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና ለጉዳዩ ቀዳሚ ትኩረት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዲኖር ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በጉባዔው የፀደቁት ሠነዶች Pact for the Future, Declaration on Future Generations, Global Digital Compact የድርድር ሂደት ላይ ተሳትፎ ስታደርግ መቆየቷን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የሠነዱ መፅደቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ድህነት፣ ረሃብ፣ የአየር ንብረት ቀውስ፣ አደገኛ ግጭቶች፣ ወረርሽኞች እና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎች እያደጉ በሚገኙበት ወቅት፣ የጋራ ምላሽ እና መፍትሄ ለመስጠት ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል።