"ጊፋታ" - የአዲስ ተስፋ ብስራትና የአብሮነት ተምሳሌት! - ኢዜአ አማርኛ
"ጊፋታ" - የአዲስ ተስፋ ብስራትና የአብሮነት ተምሳሌት!
(በፋኑኤል ዳዊት ከሀዋሳ ኢዜአ ቅርንጫፍ)
"ዮዮ ጊፋታ" ለጊፋታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን ማለት ነው። ዮዮ ጊፋታ በሚሰማበት ጊዜ በወላይታ ተወላጆች ዘንድ የሚፈጠረው ወደአዲስ ዘመን መሻገርና አዲስ ተስፋን የሚጭር ስሜት ነው። የዮ ጊፋታ ወላይታዎች አዲሱን ዓመት ለመቀበል በአዲስ ተስፋና ብስራት ከያሉበት ተሰባስበው በአብሮነት የሚያከብሩት በዓል ነው። በዓሉ ያለፈውን ዓመት ስኬትና ክፍተት በመገምገም የሚመጣውን ዘመን በተሻለ እምርታ ለመቀበል በሚያስችል የመንፈስ መነቃቃትም ይከበራል። "ጊፋታ" የአዲስ ተስፋ ብስራትና የአብሮነት ተምሳሌት የሆኑ ልዩ ቀለማትን አካቶ በአብሮነት የሚከበር በዓልም ነው።
የወላይታ ተወላጆች በያሉበት ዓመቱን ሙሉ በሥራ ካሳለፉ በኋላ ወደየአካባቢያቸውና ወደወላጆቻቸው ተመልሰው በዓሉን በአብሮነት ያከብሩታል። ሰላምና አንድነታቸውን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከአባቶችና ወላጆች እንዲሁም ከሀገር ሽማግሌዎች ምክርና ምርቃት የሚወሰድበት ነው። በመሆኑም ጊፋታ በየዓመቱ በተወላጆቹ ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። በዓሉ ወደ መልካም ነገር የመሸጋገርያ ቀን ተደርጎም ይወሰዳል።
በተለይ በዓሉ አዲስ ዘመንን መቀበልን ስለሚያበስር ይቅርታ፣ አብሮነት እንዲሁም በጋራ ተሰባስቦ ማክበር የበዓሉ ልዩ ዕሴቶች ናቸው። በመሆኑም በጊፋታ በዓል ወቅት የተጣላው ይታረቃል። ሰላምን ያወርዳል። አሮጌውን ዓመት በመሸኘት አዲሱን ዓመት በተስፋ ብርሃን መቀበል የተለመደ ነው።
ወላይታዎች በሚያካሂዱት የዘመን መቁጠሪያ መሰረት የሚከበረው "ጊፋታ" ታላቅ፣ በኩር ወይም የመጀመሪያ የሚልና መሰል ትርጓሜ አለው። በተለያዩ የጊዜ ክፍልፋዮች ዘመንን በመቁጠር የበዓሉ ቀን የሚወሰን ቢሆንም የክረምት ጭጋግ መውጫ ወቅት ተከትሎ በዓሉ ይከበራል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አበሻ ሽርኮ ጊፋታ የመጀመሪያ እንደማለት ሲሆን በዓሉም የወላይታ አባቶች እንዳስቀመጡት የክረትም ጭጋግ ወቅት መውጣትና ብርሃን የሚታይበት ወቅትን መነሻ አድርገው እንደሚያከብሩት ተናግረዋል።
ዶክተር አበሻ እንዳሉት በዓሉ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ዓመት የሚሸጋገሩበት፣ አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት እንዲሁም ለልማትና ለሰላም የሚነሱበት በመሆኑ “የሰላም ተምሳሌት” ተደርጎ ይከበራል። በበዓሉ የተጣላ ይታረቃል፣ በክረምቱ ምክንያት የተጠፋፋም ይገናኛል፣ አቅም ያለው የሌለውን ይደገፋል። በዓሉ ተሰባስበው በጋራ ማደግ እንደሚቻል የሚመከርበት ሲሆን ተበድሮ ያልከፈለ ካለም ችግሩ ተመክሮበት መፍትሄ ይሰጠዋል። በአጠቃላይ በዓሉ አዲሱን ዓመት በተስፋና በአብሮነት ለመቀበል ስንቅ የሚያዝበት ጭምር ነው።
ጊፋታ ሲከበር በዓመቱ ሰርቶ ስኬታማ የሆነና በተሻለ የመራ ሲወደስ በአንጻሩ ውጤታማ ያልሆነው ከሌላው ተሞክሮ የሚወስድበት መሆኑን የተናገሩት ዶክተር አበሻ፣ በዓሉ ዕሴት ለማህበራዊና ኢኮኖሚ እንዲሁም ሰላምን በመገንባት ልማትና ብልጽግናን ለማፋጠን ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ምህረቱ ሳሙኤልም በበኩላቸው ጊፋታ በወላይታዎች ዘንድ ከዘመን ወደዘመን ከመሻገር ባለፈ የአዲስ ተስፋና ለቀጣይ የልማት ሥራዎች መሰረት የሚጣልበት ነው ይላሉ። በተለይም ጊፋታ ሰርቶ መለወጥንና በራስ ባህል መኩራትን እንደሚያበረታታ ጠቁመው ለዚህም ተወላጆቹ የመንፈስ ጥንካሬን እንደሚላበሱ ነው የገለጹት። በጋራ የሚመከርበትና የስኬት መነሻ ተደርጎም ይወሰዳል።
በወላይታ ዘንድ ጊፋታ ሲደርስ ልዩነትን ፈትቶ እርቅ ማውረድ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። አቶ ምህረቱ እንደሚሉት ይህም በዓሉ የአብሮነትና የሰላም እሴቶች እንዳሉት ማሳያ ነው። በዓሉ ለሰላም ፣ አብሮነትና ልማትን ለማጠናከር ካለው ፋይዳ በመነሳት የአሁኑ ትውልድ ሀገር በቀል ዕውቀቱንና ትውፊቱን ከመጠቀም በላፈ ለትውልድ ጠብቆ እንዲያቆየው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የዞኑ አስተዳደር ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሰቲና የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት የጊፋታ በዓል ባህላዊ እሴቶች ይበልጥ እንዲተዋወቁና በዓሉም ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ቅርሶች መካከል እንዲመዘገብ ለማስቻል ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የሶዶ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አበበች ኤካሶ እንዳሉት ጊፋታ የሰላምና ዕርቅ እንዲሁም ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ እና ጎረቤት የሚጠያየቅበት በዓል ነው። በዚህም አብሮነትና ሰላም ይጠነክራል፤ በሂደቱም አንዱ ከሌላው የስኬት ልምድን ይቀስማል፤ ከድክመቱም ይማራል።
በበዓሉ ላይ ከሚከናወኑ ሁነቶች መካከል በዋናነት የአባቶች ምርቃትን የጠቀሱት ወይዘሮ አበበች ወጣቶች ነገአቸው የሰመረ እንዲሆን በአባቶች ይመረቃሉ። ልጆች በበዓሉ ወቅት ወደቤተሰቦቻቸው እንዲሰባሰቡ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች አንዱ ይሄው የምረቃ ሥነስርአት እንደሆነም ነው የገለጹት።
ምረቃው ሲካሄድ በዓመቱ ሰርቶ የተሳካለትን በማሞገስና ያልተሳካለትን ደግሞ በመምከር ለቀጣይ በአዲስ ተስፋ ለስራ እንዲነሳሱ ይደረጋል። በመሆኑም “ጊፋታ የአዲስ ተስፋ ብስራት“ ተደርጎ ይወሰዳል። በምድር ስትኖር “ወልደህ ከወግ ማዕረግ ለማድረስ፣ ሰርተህ ለስኬት መብቃትና ልቀህ መታየት ትመኛለህ ያሉት ወይዘሮ አበበች ጊፋታ ከእነዚህ ሁሉ ጋር የተያዘ ስለሆነ በተለይም ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለማሸነፍና በራሱ የሚኮራ ትውልድ ከማፍራት አንጻር ልዩ ትርጉም እንዳለው ነው የገለጹት።
የወላይታ ሀገር ሽማግሌ አቶ ሚልክያስ ኦሎሎ በበኩላቸው እንዳሉት የጊፋታ በዓል የአዲስ ተስፋ ብስራት ነው። እሳቸው እንዳሉት የበዓሉ ዕሴት አዲስ ዘመንን በቂምና ቁርሾ መቀበልና መሻገር አይቻልም። በመሆኑም በግለሰብ ብቻ ሳይሆን በመንግስትና ህዝብ መካከል እንኳ ችግሮችና አለመግባባቶች ቢኖሩ በዓሉን የሚቀበሉት ተነጋግሮ ችግሮችን በመፍታትና በዕርቅ ነው። ይህም ቀጣይ ጊዜን በአብሮነትና በሰላም ለማሳለፍ ጉልህ ሚና አለው። ለእዚህም ነው ጊፋታ የአዲስ ተስፋ ብስራትና የአብሮነት ተምሳሌት የሚያደርገው።
"በዓሉ ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ክዋኔዎች የሚታሰብ ነው" ያሉት አቶ ሚልክያስ በተለይም ለሰላምና ለአብሮነት የሚሰጠው ቦታ ልዩ መሆኑን ነው የገለጹት። ይህም ሰላማዊ አካባቢ በመፍጠር ዜጎች ልማት ላይ እንዲያተኮሩ ያደርጋል ባይ ናቸው።
የወላይታ ዞንም ሰላማዊ ሆኖ ልማቱ ላይ ብቻ እንዲያተኮር የጊፋታ ዕሴት የጎላ አስተዋጾ እንዳለው ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት ትውልዱ ባህሉን ይበልጥ እንዲያውቅና እንዲረዳ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች መጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል በተለያዩ ክዋኔዎች ታጅቦ በድምቀት እየተከበረ ነው።
ዮዮ ጊፋታ!