ቀጥታ፡

በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ አስደናቂ ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶችን በስፋት በማስተዋወቅ የሀገር ሃብት የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2017(ኢዜአ)፦በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ አስደናቂ ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶችን በስፋት በማስተዋወቅ የሀገር ሃብት የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የቦሮ ሺናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ "ጋሪ ዎሮ" በዓል የብሔረሰቡ ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከብሯል፡፡

በየዓመቱ የአዲስ ዓመት መግባትን ተከትሎ በተለያዩ ዝግጅቶች የብሔረሰቡ ተወላጆች የሚያከብሩት የዘመን መለወጫ በዓል "ጋሪ ዎሮ" ይባላል፡፡ 

የበዓሉ አከባበር ስለ ህዝቦች አብሮነት፣ ሰላምና አንድነት የሚነገርበት እንዲሁም ከፈጣሪ ምህረት የሚለመንበት መሆኑም ይነገራል። 

በዚሁ መሰረትም በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።

በሁነቱ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይ አህመድ መሃመድ፤ የጋሪ ዎሮ በዓል የአንድነት፣ የመቻቻል እና የአብሮነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የበዓሉን እሴቶችና ትውፊቶች በመጠበቅና በማክበር ለትውልድ በማስተላለፍ የሀገርን አንድነት ማፅናትና አብሮነትን ማዝለቅ ይገባል ብለዋል። 

በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ አስደናቂ ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶችን በስፋት በማስተዋወቅ የሀገር ሃብት የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቦሮ ሺናሻ ማህበረሰብ የሀገር ሽማግሌ አቶ አዲሱ አዳሜ፤ በዓሉ የመልካም ምኞት መግለጫ እና የሰላም ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰው በይቅርታ፣ በፍቅርና መተሳሰብ ሁሉም በንጹህ ልብ ወደ አዲስ ዓመት የሚሸጋገርበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተስፋሁን ኪሉ እና ድንቅነሽ ሙለታ፤ ጋሪ ዎሮ በክረምቱ ውሃ ሙላት ሳቢያ ተራርቀው የነበሩ ሰዎች የሚገናኙበት በብዙዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ አስደናቂና ተናፋቂ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዓሉ ያለ ቋንቋና ዕድሜ ልዩነት በጋራ የሚከበር የሰላምና የፍቅር መገለጫ ስለመሆኑም አንስተዋል። 

በተያዘው የመስከረም ወር በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላቸውን በተለያዩ ቦታዎች በማክበር ላይ ይገኛሉ። 

ለአብነትም በዛሬው ዕለት ከቦሮ ሺናሻ ብሔረሰብ በተጨማሪ የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል " ዮዮ ጊፋታ " በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም