ቀጥታ፡

ምርኩዝ የትምህርትና በጎ አድራጎት ማህበር  ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ባህርዳር፤ መስከረም 12/2017 (ኢዜአ)፦ ምርኩዝ የትምህርትና በጎ አድራጎት ማህበር በባህርዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የማህበሩ አስተባባሪ ወጣት ሽኩር አህመድ እንደገለፀው ማህበሩ "የእኛ ለእኛ" በሚል መሪህ ድጋፉን ያደረገው በባህርዳር ከተማ ከሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ለ750 ችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች ነው።

ለእያንዳንዱ ተማሪም ደርዘን ደብተር፣ እስክርቢቶ፣ እርሳስ፣ መቅረጫ፣ ላጲስ እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግሯል።

ሀገር የምታደገውና የምትበለፅገው የተማረና የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት ሲቻል ነው ያለው ወጣት ሽኩር፤ ድጋፉም የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆች ሳይቸገሩ ተምረው ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ ለማገዝ ነው ብሏል።

ማህበሩ ከሚያደርገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ ለ150 የተቸገሩ ቤተሰቦች በየወሩ ከ750 እስከ 1 ሺህ 500 ብር በቋሚነት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ወጣት ሽኩር አስታውቋል።

በባህርዳር ከተማ አስተዳደር የፋሲል ክፍለ ከተማ የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ የውልሰው አሰፋ እንዳሉት ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገት መፋጠን ጉልህ አበርክቶ አለው ።

የሀገር ዕድገት ሊፋጠን የሚችለው የተማረ ዜጋ ሲኖር ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ለዚህ እንዲያግዝም ማህበሩ ባለፉት አራት ዓመታት የተቸገሩ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ይህንን በጎ ተግባር ሌሎች ባለሃብቶች በአርአያነት ወስደው ትውልድን ለመቅረፅና ለመገንባት ሊተገብሩት እንደሚገባም ወይዘሮ የውልሰው አሳስበዋል።

የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ በርትተን በመማር ትልቅ ደረጃ እንድንደርስ የግዘናል  ያለው ደግሞ የጊዮን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህር ቤት የ10ኛ ክፍል አካል ጉዳተኛ ተማሪ አቤል አየነው ነው።

ሌላኛው የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሃብተማርያም ፈንታ በበኩሉ ላለፉት አራት ዓመታት ማህበሩ በሚያደርግለት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ትምህርቱን ሳይቸገር እየተማረ እንደሚገኝ ገልጿል። 

በቀጣይ ጠንክሮ በመማርና ትልቅ ደረጃ በመድረስ ችግረኛ ተማሪዎችን በማገዝ የዜግነት ድርሻውን ለመወጣት ዓላማ እንዳለውም አስታውቋል።

ያገኘሁት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ  ከወዲሁ ትምህርቴን በርትቼ በመማር ትልቅ ደረጃ እንድደርስ ያግዘኛል ያለችው ደግሞ የአፄ ሰርፀ ድንግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የ2ኛ ክፍል ተማሪ ሠዓዳ አህመድ ናት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም