ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሴቶች ፎረም በማህበራዊ ልማትና አመራር ያላትን ተሞክሮ አቀረበች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሴቶች ፎረም በማህበራዊ ልማትና አመራር ያላትን ተሞክሮ አቀረበች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/ 2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሩሲያ በተካሄደው አራተኛው የአውሮፓና እስያ አገራት የሴቶች ፎረም( Eurasian women Forum) በማህበራዊ ልማትና የሴት አመራሮች ተሳትፎ ያላትን ተሞክሮ አቅርባለች።
በፎረሙ ላይ የብሪክስ አባል አገራትን ጨምሮ ከ126 ሀገሮች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ተሳትፎ አድርጓል።
በፎረሙ 'የማህበራዊ ልማትና ሴቶች' በሚል ርዕስ በተደረገ ውይይት ኢትዮጵያን ተሞክሮዋን አቅርባለች።
በፎረሙ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ወክለው በተገኙ አመራሮችም 'ሴቶችና አመራር' በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ከአራተኛው የአውሮፓና እስያ አገራት ሴቶች ፎረም ጎን ለጎን በተካሄደው የብሪክስ የሴቶች ፎረም ላይ ተሳትፋለች።
ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል አገርነቷ የትብብርና ቅንጅት ስራዎችን በተመለከተም ተሞክሮዎችን ከመለዋወጥ ባሻገር በጋራ ሊተገበሩ የሚችሉ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችም ታሳቢ መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች ተነስተዋል።
አባል ሀገራት የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን በማምጣት ረገድ የተሞክሮ ልውውጥ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በየሀገራቱ የሚተገበሩ ስትራቴጂዎች፣ የወጡ የህግ ማዕቀፎችና ፕሮግራሞች ቀርበው ውይይት ተካሄዷል።
ፎረሙ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ማካፈልና ከሌሎችም ጠቃሚ ልምዶችን መውሰድ የተቻለበት እንደሆነ ተገልጿል።
በፎረሙ ላይ በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል የትብብርና የአጋርነት ስራዎች፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነት ለማረጋገጥና ሴቶችን ለማብቃት የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሱን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።