የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2017(ኢዜአ):-የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት አከባበርን አስመልክቶ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሕዝብ ውይይት አካሂዷል።
የውይይቱ ተሳፊዎች የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት በየዓመቱ በጉጉት የምንጠብቃቸው የመዲናችን ድምቀቶች ናቸው ብለዋል።
የመስቀልና እሬቻ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አስተያየት ሰጪዎች የሠላም ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የመስቀልና ኢሬቻ በዓት የኢትዮጵያውን የአንድነትንና የወንድማማችነትን ማስተሳሰሪያ ገመዶች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
በመሆኑም እነዚህ በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ ከጸጥታ ኃይሉ በተጨማሪ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በአካባቢያቸው የሚገኝ የጸጥታ ኃይል በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት በዓላቱ በሰላምና በፍቅር እንዲከበሩ በትበብር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በበኩሉ ፥ ከአደባባይ በዓላት መካከል የሚመደቡት የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን አድርጓል።
እንግዶችን የሚቀበል፣ የሰላሙን ሁኔታ የሚመራ እንዲሁም ሌሎች ለበዓሉ ድምቀት የሚሆኑ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ኮሚቴዎች ከከተማ እስከ ብሎክ ድረስ ተደራጅተው ሥራ ጀምረዋል ነው የተባለው።