ማንችስተር ሲቲና አርሰናል በፕሪሚየር ሊጉ የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ሲቲና አርሰናል በፕሪሚየር ሊጉ የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2017 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ30 ላይ በኢቲሃድ ስታዲየም ይደረጋል።
የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ማንችስተር ሲቲና አርሰናል በቅርብ ዓመታት ውስጥ እያሳዩት ያለው ተቀናቃኝነት የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።
ሁለቱ ክለቦች እስከ አሁን በሁሉም ውድድሮች 211 ጊዜ ተገናኝተዋል።
አርሰናል 99ኙን በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ማንችስተር ሲቲ 35 ጊዜ አሸንፏል። 47 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ (በቀድሞ የውድድር ፎርማት የመጀመሪያ ዲቪዚዮንን ይጨምራል) 54 ጊዜ ተገናኝተው አርሰናል 24 ጊዜ ሲያሸንፍ ማንችስተር ሲቲ 19 ጊዜ ድል ቀንቶታል።
11 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
የ53 ዓመቱ ስፔናዊ የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይደረጋል ብሎ እንደሚጠብቅ ገልጾ ግጥሚያው የሊጉን አሸናፊ የሚወስን አይደለም ሲል ከጨዋታው በፊት በሰጠው መግለጫ ተናግሯል።
የ42 ዓመቱ ስፔናዊ የአርሰናል አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ለሚደረገው ወሳኝ ጨዋታ ከቅድመ ውድድር ጊዜ አንስቶ ስንዘጋጅ ነበር፣ ቡድኑ ለጨዋታው በአካል ብቃት፣አእምሮና በታክቲክ ዝግጁ መሆኑን በሰጠው አስተያየት ገልጿል።
የ39 ዓመቱ ማይክል ኦሊቨር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።