ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሰናበተ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2024/25 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር በደርሶ መልስ ውጤት ተሸንፎ ወደ ምድብ ድልድሉ መግባት ሳይችል ቀርቷል።

ያንግ አፍሪካንስ በውድድሩ ወደ ምድብ ድልድሉ ማለፍ ችሏል። ንግድ ባንክ በዛንዚባር በሚገኘው አማኒ ኮምፕሌክስ ስታዲየም ዛሬ ማምሻውን ባደረገው የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ በታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ 6 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ተሸንፏል።

የ28 ዓመቱ አጥቂ ስቴፋን አዚዝ ኪ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል። ክሌመንት ሚዚዜ፣ ክላቶስ ቻማና ሙዳቲሪ ያህያ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ያንግ አፍሪካንስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በአጠቃላይ ውጤት 7 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ምድብ ድልድሉ መግባቱን አረጋግጧል። ንግድ ባንክ መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም በአበበ በቂላ ስታዲየም ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ 1 ለ 0 መሸነፉ ይታወቃል።

በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ በታሪኩ የመጀመሪያ ተሳትፎውን ያደረገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንደኛው ዙር የዩጋንዳውን ቪላ ክለብ 3 ለ 2 በሆነ ድምር ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ያገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም