ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2017(ኢዜአ):- የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን  ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት አከባበርን አስመልክቶ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሕዝብ ውይይት አካሂዷል።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳፊዎች የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት በየዓመቱ በጉጉት የምንጠብቃቸው የመዲናችን ድምቀቶች ናቸው ብለዋል። 

እነዚህን በዓላት እሴታቸው ተጠብቀው እንዲከበሩ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን ነው ያሉት። 

አቶ አጥናፉ ገመቹ፤ መስቀልና እሬቻ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። 

ከእርሳቸው ባሻገርም ልጆቻቸውና የአካባቢያቸው ወጣቶች ለበዓሉ ድምቀት የበኩላቸው አስተዋጾ እንደሚያበረክቱ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

ሀደ ስንቄ ወይዞሮ አረጋሽ ገዳ በዓላቶቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ ሁላችንን ተባብረን መሥራት አለብን ብለዋል። 

ፓስተር ሙሉጌታ ስዩም የሠላም ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰው ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላት ሊጋለጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

ወይዘሮ እጅጋየሁ አበራ በበኩላቸው፤ መስቀልና ኢሬቻ የእኛ ኢትዮጵያውን የአንድነትንና የወንድማማችነትን ማስተሳሰሪያ ገመዶች ናቸው ብለዋል። 

በመሆኑም እነዚህ በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ ከጸጥታ ኃይሉ በተጨማሪ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ  በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

በአካባቢያቸው የሚገኝ የጸጥታ ኃይል በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት በዓላቱ በሰላምና በፍቅር እንዲከበሩ በትበብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

በበዓሉ ወቅት ምንአልባት የሚያውኩ እንቅስቃሴዎች እንዳይኖሩ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ተዎድሮስ ሽፈራው ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የገበያ ዘርፍ ኃላፊ ፍስሃ ጥበቡ በበኩላቸው፡ በበዓላቱ ወቅት የገበያ እጥረት እንዳያጋጥም እሁድ ገበያንና ባዛሮችን ጨምሮ የተለያዩ የገበያ አማራጮች መዘርጋታቸው አመላክተዋል። 


 

ከአደባባይ በዓላት መካከል የሚመደቡት የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጾል። 

እንግዶችን የሚቀበል፣ የሰላሙን ሁኔታ የሚመራ እንዲሁም ሌሎች ለበዓሉ ድምቀት የሚሆኑ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ኮሚቴዎች ከከተማ እስከ ብሎክ ድረስ ተደራጅተው ሥራ መጀመራቸውን ተመላክቷል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም