ታዳጊዎች ያላቸውን ችሎታ የሚያጎለብቱበት ምቹ የስፖርት አካዳሚዎች ሊስፋፉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ታዳጊዎች ያላቸውን ችሎታ የሚያጎለብቱበት ምቹ የስፖርት አካዳሚዎች ሊስፋፉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2017(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ታዳጊዎች ያላቸውን ችሎታ የሚያጎለብቱበት ምቹ የስፖርት አካዳሚዎች እንዲስፋፉ ተጠየቀ።
በ2017 ዓ.ም ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ 196 ታዳጊዎችን ተቀብሎ በልዩ ልዩ የስፖርት አይነቶች እንደሚያሰለጥን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ገልጿል።
ይህንን ተከትሎም አካዳሚው ከሐምሌ 25 ቀን እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ፤ አካዳሚውን የሚቀላቀሉ ታዳጊ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጀመሪያውን ዙር የእጩ ምልመላ ሲያካሄድ ቆይቷል።
ሁለተኛውን (የመጨረሻው) ምልመላ አካዳሚው በመጀመሪያው ዙር በልዩ ልዩ መስፈርቶች ከመረጣቸው 594 ታዳጊዎች መካከል የመምረጥ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
የመጨረሻው ዙር የምልመላ ሂደት ካሳለፍነው መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአካዳሚው እየተካሄደ ሲሆን በነገው ዕለት መረጣው እንደሚጠናቀቅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢዜአም ታዳጊዎቹ ያላቸውን የስፖርት ብቃት በመፈተሽ ወደ አካዳሚው ለመግባት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲሁም የመወዳደር እድሉን ማግኘታቸው ያስገኘላቸውን ጠቀሜታ በተመለከተ ከተለያየ ክልል የመጡ ታዳጊዎችን አነጋግሯል።
ምህረት ሰለሞን የ16 ዓመት ታዳጊ ስትሆን ከአርባ ምንጭ ከተማ ለእግር ኳስ ካላት ልዩ ፍላጎት አኳያ ያላትን ብቃት ለማሳደግ ወደ አካዳሚው መግባት የሚያስችላትን የመጀመሪያ ዙር ውድድር በማለፍ ለመጨረሻ ዙር ውድድር በአካዳሚው መገኘቷን ተናግራለች።
በዚህም በስፖርት ዘርፉ ያላትን ብቃት የምትፈትሽበት የውድድር መድረክን በቀላሉ በማግኘቷ መደሰቷን ገልጻ በአካባቢው ፍላጎቱ ኖሯቸው እድሉን ያላገኙ ታዳጊዎች መኖራቸውን ትገልጻለች።
ለዚህም ምክንያት ከሆኑት ውስጥ የስፖርት አካዳሚዎች በክልሎች በስፋት ያልተስፋፉ መሆናቸው አንዱ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ይህ ችግር እንዲቀረፍ መንግሥትና ባለኃብቶች ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጠይቃለች።
ሌላኛው ከሀረር ከተማ የመጣው የ16 ዓመት ታዳጊ አቤነዘር ማሙሽ በበኩሉ ለቦክስ ካለው ፍቅር ወደ አካዳሚው መግባት የሚያስችለውን መስፈርት ለማሟላት ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ሀገራችን ለስፖርት ዘርፉ እድገት የሚኖረንን አበርክቶ ለመጨመር በየክልሉ ምቹ የማሰልጠኛ እና ማዘውተሪያ ስፍራዎችና አካዳሚዎች ሊስፋፉ እንደሚገባ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከሀዋሳ በቅርጫት ኳስ ስፖርት ለመጨረሻ ዙር ለመወዳደር የመጣችው የ17 ዓመቷ ሀና ታምራት በበኩሏ በአካባቢዋ አርሷም ሆነች የእድሜ እኩዮቿ ያላቸውን የስፖርት ችሎታ የሚያጎለብቱበት የስፖርት ማዘውተሪያዎች ቢኖሩም በቂ አለመሆኑን ገልጻለች።
በስፖርቱ ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት ታዳጊዎች በአግባቡ ያለምንም ኃሳብ የምንሰለጥንባቸው አካዳሚዎች ሊጠናከሩ ይገባል ብላለች።
በኢትዮጵያ የስፖርት አካዳሚ የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ዲን ጎሳ ሞላ በበኩላቸው አካዳሚው በ2017ዓ.ም ተቋሙን የሚቀላቀሉ ታዳጊ ስፖርተኞችን ለመመልመል ከተለያዩ ቦታዎች ከመዘገባቸው 850 ታዳጊዎች መካከል 594 የሚሆኑትን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ የመጨረሻ ዙር ምልመላ ማካሄድ ጀምሯል ብለዋል።
594ቱ ብቻ ጥሪ የተደረገላቸው ምክንያት በየክልሉ በምዝገባ በመጀመሪያ ዙር የተመረጡ ታዳጊዎችን ስፖርቱ የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልተዋል የሚለውን ነገር ከአጠቃላይ ተመዝጋቢ ታዳጊዎች ጋር በማነጻጸር ነው ብለዋል።
ነገር ግን ወደ አካዳሚው ለመጨረሻው ዙር ውድድር ጥሪ አልተደረገላቸውም ማለት ስፖርት አይችሉም ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
በአጠቃላይ በ2017 ዓ.ም ከተለያዩ ክልሎች 196 ታዳጊ ስፖርተኞች በመምረጥ አካዳሚው ተቀብሎ ለአራት ዓመት በልዩ ልዩ ስፖርት ዘርፎች እንደሚያሰለጥን ገልጸዋል።
ሀገሪቱ ከስፖርት ዘርፍ ማግኘት ያለባትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ታዳጊዎችን ከህጻንነታቸው ጀምሮ ስለ ስፖርት በቂ እውቀትና ችሎታው እንዲኖራቸው ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራን አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተቋቋመበት 2005ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ብቁ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።