ምሩቃን በቀሰሙት ዕውቀት ችግር ፈቺ በመሆን የአገሪቱን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ምሩቃን በቀሰሙት ዕውቀት ችግር ፈቺ በመሆን የአገሪቱን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
ባህርዳር ፣ መስከረም 11/2017 (ኢዜአ)፦ ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት ዕውቀት ችግር ፈቺ በመሆን ከራሳቸው አልፈው የአገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።
"ጅግዳን " ኮሌጅ የባህርዳር ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በደረጃ አራት፣ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 723 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡
በምረቃው ስነ-ሰርዓት ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ አለሙ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አገርን ለማበልፀግና ለማሳደግ የበቃና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ትምህርት ዋነኛ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
"ጅግዳን" ኮሌጅ ጥራቱ የተረጋገጠ ትምህርት በመስጠት ገበያው የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት እያደረገ ያለው የበኩሉን ጥረት መልካም መሆኑን አመልክተዋል።
የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎችም በትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት ዕውቀት ችግር ፈቺ በመሆን ከራሳቸው አልፈው የአገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የጅግዳን ኮሌጅ ዲን አቶ አማኑኤል መኮንን በበኩላቸው፤ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማስጠበቅ መንግስት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ ኮሌጁ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሌጁ ዛሬ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በደረጃ አራት፣ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛው፣ በማታውና በርቀት መርሃ ግብሮች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 723 ተማሪዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከልም 343 በሁለተኛ ዲግሪ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ደግሞ 392 ሴቶች እንደሆኑም ጠቁመዋል።
በተማረበት የትምህርት መስክ ስራ ፈጣሪ በመሆን ከራሱ አልፎ አገሩን ለመጥቀም መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ በ"ቢዝነስ አድምንስትሬሽን "የትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪውን የተመረቀው በለጠ አድማሴ ነው።
አሁን እየሰራ በሚገኙበት የባንክ ኢንዱስትሪ በተለይ ተበዳሪ ወገኖች በሚወስዱት ብድር ውጤታማ ስራ ሰርተው እንዲለወጡ የማማከር ድርሻውን ለመወጣት እንደሚጥር ተናግሯል።
ኮሌጁ የዛሬ ተመራቂዎችን ጨምሮ እስካሁን 23 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች አሰልጥኖ ማስመረቁም ተመልክቷል።