በመስከረም ወር የሚከበሩ በዓላት ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች የቆይታ ጊዜን ለማራዘም ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2017(ኢዜአ):- በመስከረም ወር የሚከበሩ በዓላት ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች የቆይታ ጊዜን ለማራዘም የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች እና የቱሪስት መስህቦች አሏት፡፡

የመስከረም ወር ከዘመን መለወጫ ጀምሮ የተለያዩ በዓላት በስፋት የሚከበሩበት ወር መሆኑ ይታወቃል፡፡

በየዓመቱ እነዚህን ክብረ በዓላት ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡

ጎብኚዎች የቱሪዝምን እድገት በማጠናከር፣ ታሪክ፣ ቅርስ እና የህዝብን ባህል ወግና ልማድ ለዓለም በማስተዋወቅ የጎላ አበርክቶ አላቸው፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች የበለጸገች ቢሆንም በቂ የቱሪዝም መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች፡፡

ከለውጡ በኋላ መንግሥት ቱሪዝምን ከአምስቱ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ በማድረግ በዘርፉ በርካታ ሥራዎች እንዲከናወኑ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን ከማልማት ባሻገር ነባሮችን ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡

መስከረም ወር የተለያዩ ሐይማኖታዊና ሐይማኖታዊ ያልሆኑ በዓላት የሚከበሩበት ወቅት መሆኑን ገልጸው፤ በርከት ያሉ የውጭ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ብለዋል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ በዓላቱን ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ በማክበር የባህል ልውውጥ ከመፍጠር ባለፈ፤ ከተለያዩ ሀገራት ለሚመጡ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ሊያስተዋውቅበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት ህዝባዊ በዓላት የሰላምና የአንድነት መገለጫዎች እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር የውጭ ጎብኚዎች የተራዘመ ቆይታ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ የበዓላት ጥቅል አገልግሎቶችን አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ሚኒስቴሩ ከክልሎችና ከሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲተዋወቁ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ከአንድ ሚሊየን በላይ የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ እቅድ መያዙን ገልጸው፤ ለመዝናናት፣ ለኮንፍረንስ፣ ለኤግዚቢሽንና ሌሎች ዓላማዎች የሚመጡ እንግዶችን ቆይታ ለማራዘም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሃብቶች በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሁነቶች በስፋት ሲተዋወቁ እንደነበር ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገቢ ለማስፋት የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም