ሆቴሎችና አስጎብኚዎች ለመስከረም ክብረ በዓላት እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ሆቴሎችና አስጎብኚዎች ለመስከረም ክብረ በዓላት እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2017 (ኢዜአ)፦ ለመስከረም አደባባይ ክብረ በዓላት እንግዶችን በቅጡ ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጋቸውን ሆቴሎች እና አስጎብኚዎች ገለጹ።
መስከረም የባለ 13 ወራት ጸጋዋ ሀገር ኢትዮጵያ ውብ መልኮች መታያ ወር ነው።
ከመልክዓ ኢትዮጵያ መገለጫዎች አንዱ የሆነው የዘመን መለወጫው መስከረም በየዓመቱ ሲጠባ አሮጌ ዘመን ሸኝቶ፣ የአዲስ ዘመን ፍካት ሰንቆ በመሆኑ፤ ምንጊዜም ተናፋቂ ወር ነው፡፡
ምድር የውበት አክሊል የምትደፋበት፣ የእንስሳት የተድላ ጊዜ፣ ሰዎች ብሩህ ተስፋ የሚሰንቁበትም ወቅት ነው፡፡
የደመራና መስቀል ጨምሮ የመሥከረም የአደባባይ ክብረ በዓላት ትዕይንቶችና ክዋኔዎች ሀገረኛ ባሕል፣ እሴትና ትውፊት የሚያንጸባርቁበት ብሎም ታሪክና ቅርሷ በአደባባይ የሚገልጡ ናቸው፡፡
የመስከረም መልኮች ሀገሬውን ብቻ ሳይሆን የጎብኚዎችን ቀልብ ይስባሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ቦርድ አባል ዮናስ ትኩ የመስከረም ውብ መልኮች ለቱሪዝም ዘርፍ ልዩ አስተዋጸኦ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
የዓለም የቱሪዝም ቀን ከመስቀል በዓል ጋር መጣጣሙም መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የታላቅ ኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማህበር ቦርድ አባል ናሆም አድማሱ መስከረም በርካታ የአደባባይ ክብረ በዓላት የሚከበሩበት በመሆኑ ለኢትዮጵያ መድመቂያ ወርኅ ነው ይላሉ።
የማህበሩ አባላት በዘንድሮ ክብረ በዓላት ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ቱሪስቶችን በመቀበል በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ተዘዋውረው በዓላቱን እንዲያከብሩ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የቴማ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማኅበር ሥራ አሥኪያጅ ቴዎድሮስ ሰለሞን የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነውን መስቀል እና ኢሬቻ ክብረ በዓላት እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ማህበሩ በበይነ መረብ አማራጮች በመጠቀም መረጃ ማጠናቀሩንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ከውጭ የሚመጡ እንግዶች በዓላትን የሚታደሙበት ልዩ መግቢያ ማዘጋጀቱን አመልክተዋል።
የሆቴልና መሰል አገልግሎቶች አሰሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት(ዶ/ር)፣ ሆቴሎች ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት ታዳሚ እንግዶችን ለማስተናግድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች የሚገኙ የቱሪዝም ዘርፍ ተዋንያን እንግዶችን የሀገር ክብርና ገጽታን በሚያጎላ መልኩ እንዲያስተናግዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የመልካ ሆቴል የኦፕሬሽን ማናጀር ነብዩ በለጠ እንግዶች የሀገር ገጽታና ክብርን በሚያሳይ መልኩ ለማስተናግድ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።