ያ ሆዴ የአዲስ ብርሃን ተስፋ - ኢዜአ አማርኛ
ያ ሆዴ የአዲስ ብርሃን ተስፋ
በማሙሽ ጋረደው ከሆሳዕና የኢዜአ ቅርንጫፍ
ከብት የሚጠብቁ ህፃናት አዲስ ዓመት እየመጣ ስለመሆኑ ማብሰሪያ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የዋሽንት /የገምባቡያ/ ድምፅ ማሰማት ይጀምራሉ። በመስከረም ከጉምና ጭጋግ ፀለምት ጨለማ የሚወጣበትና ምድሩ በአበባ ሀምራዊ ቀለም የሚታጀብበት ወቅት በመሆኑ በሀዲያ ብሄር ዘንድ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ወቅት ነው። ያ ሆዴ የሀዲያዎች አዲስ የዘመን መለወጫ በዓል መባቻ ነው።
ያ ሆዴ ማለት በሀዲያዎች ዘንድ “ብርሃን ሆነ፣ መስቀል መጣ፣ ገበያው ደራ፣ በይፋ ተበሰረ ብሎም እንኳን ደስ አላችሁ” የሚል ስያሜ እንዳለውም ይነገራል። “ያ ሆዴ " በሀዲያ ካሉ እሴቶችና ወጎች እንዲሁም ክንዋኔዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ አንድነት፣ መቻቻል፣ ለውጥን ለማሳለጥ፣ አብሮነትና ሰላም ለማጠናከርም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይወሳል።
የሀዲያ አገር ሽማግሌ አቶ መንገሻ ሂቤቦ እንዳጫወቱን ከሆነ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ከብት የሚጠብቁ ህፃናት አዲስ ዓመት መምጣቱን የዋሽንት /የገምባቡያ/ ድምፅ በማሰማት አዋጅ ማብሰር ይጀምራሉ። ይህም የበዓሉ መቅረብን ለማሳሰብና ለማስታወቅ የሚደረግ ነው። በዓሉ ብርሃን፣ብሩህ ተስፋ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ረድኤት በረከት የሚሞላበት ተምሳሌታዊ ወር ተደርጎ ይታመናል።
ያ ሆዴ በሀዲያ ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው በዓል ነው። በዓሉ ከመድረሱ በፊት ሁሉም የቤተሰብ አባላት በዓሉን ለማድመቅ የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። ለምሳሌ አባት ለእርድ የሚሆን ከብት በማቅረብ፣ እናት ደግሞ ሌሎች የቤት ስራዎች በማከናወንና ልጆችም ልዩ ልዩ የስራ ድርሻቸውን በመወጣት በዓሉን ያከብራሉ።
“አባቶች አብሮነታቸውን ከሚያጠናክሩባቸው ማህበራዊ እሴቶች መካከል አንዱ ቱታ /ሼማታ/ ነው” ይላሉ የሀዲያ አገር ሽማግሌ አቶ መንገሻ፤ ይህም ከአራት አስከ ስምንት አባላትን ይዞ የሚደራጅ የስጋ ማህበር ነው። የማህበሩ አባላት ግንኙነት ያላቸው የሚተሳሰቡ የኢኮኖሚ አቅማቸውም ተቀራራቢነት ያለው ሲሆን፤ በዓሉ ከመድረሱ በፊት በጋራ ገንዘብ ማስቀመጥ ይጀምራሉ።
ለስጋ መብያ የሚሆን ቆጮ ብሎም ለአተካና የሚሆን ቡላ በማዘጋጀት ከጥቅምት እሰከ ጥር ባሉት ወራት ውስጥ እንሰት በመፋቅ እናቶች በቡድን ተሰባስበው ዝግጅታቸውን ማከናወን ይጀምራሉ። በተጨማሪም ዊጆ |የቅቤ እቁብ| በመግባት ቅቤ በማጠራቀም ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ቅመማ ቅመሞችን በማዘጋጀት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። የዳጣ፣ የአዋዜ ዝርያዎችንና ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑ ባህላዊ የሆኑ መጠጦችን ጭምር ያዘጋጃሉ።
ልጃገረዶች በዓሉ እንዲደምቅ ቤት መደልደል፣ የተለያዩ ቀለማትን በመጠቀም የግርግዳ ቅርጻ ቅርጾችን በመስራት እንዲሁም ግቢ በማጽዳት የማሳመር ስራቸውን ያከናውናሉ። ወጣት ወንዶች ለማገዶ የሚያገለግል በአባቶች ተለይቶ የተሰጣቸውን እንጨት ፈልጠው እንዲደርቅ ያደርጋሉ። ጦምቦራ ለደመራ የሚሆን ችቦ በማዘጋጀት ግዴታቸውን ይወጣሉ።
የሀዲያ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ባለሙያ ወይዘሮ አመለወርቅ ሃንዳሞ እንደሚሉት፤ በዓሉን ለማክበር በአገር ውስጥ የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለስ አብሮነት ለማክበር ከእሩቅም ከቅርብም ይሰበሰባሉ።
ይህም በዓሉ ለአብሮነትና ለሰላም ያለውን ፋይዳ የላቀ ያደርገዋል። ዓመቱን ሙሉ ለበዓሉ የሚደረጉ ዝግጅቶችና የስራ ክፍፍሎች ልዩ ትርጉም ያላቸው ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ “ወጣቶች የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት በመሆኑ በዓሉን ልዩ ድባብ ይሰጠዋል” ይላሉ ወዘሮ አመለወርቅ።
የበዓሉ ዋዜማ /ፉሊት ሂሞ/ ወጣቶች ያዘጋጁትን ጦምቦራ /የደመራ ችቦ/ የአካባቢውን ነዋሪዎች በሚያዋስን ቦታ ላይ ይሰራሉ። እናቶች ከቡላ፣ ቅቤና ወተት የሚያዘጋጁት ጣፋጭ የሆነ እና ጣት የሚያስቆረጥመውን አተካና በማዘጋጀት የበዓሉን ዋዜማ/ፉሊት ሂሞን/ ያደምቁታል። የበዓሉ አመሻሽ ዋዜማ ላይ ወጣቶች “ያ ሆዴ ያ ሆዴ “በማለት ይጨፍራሉ። ይህም ለበዓሉ “የእንኳን አደረሳችሁ” መልእክት አለው።
በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የአገር በቀል እውቀቶች ምርምር ዳይሬክተር አቶ እያሱ ጥላሁን “ይህ በዓል የሚሰጠው የስራ ክፍፍል፣ የሰላምና አብሮነት ዕሴቶች ለጠንካራ ዕድገት፣ ነገን በተስፋ ለመመልከት ወሳኝ ነው” በማለት ይገልጹታል።
በወቅቱ ወጣቶች በአካባቢው እየዞሩ በመጫወት ከአባቶች ምርቃት ይቀበላሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ደመራው በተዘጋጀበት ቦታ ማምሻውን ይሰባሰቡና አባቶች ደመራውን የሚያቀጣጥሉበትን ችቦ በመያዝ ልጆችን በማስከተል ዓመቱ የብርሃን፣ የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ እንዲሆን ፈጣሪያቸውን በመማጸን ደመራውን ይለኩሳሉ። ደመራው ተቀጣጥሎ እንዳለቀ በእድሜ ከፍ ወዳሉ አባወራ ቤት እንደሚሰባሰቡ ነው አቶ እያሱ የተናገሩት።
የእርድ ስርዓቱ በሚከናወንበት ቤት ደጃፍ አባላቱ ቤተሰቦቻቸውን በመያዝ በአንድነት በመሰባሰብ የጋቢማ ስርዓት ይከናወናል። ይህም እድሜ ጠገብ ሽማግሌዎች ቅቤ እና ወተት በሚታረደው በሬ ላይ እያፈሰሱ” ለምለም ሳር "በመያዝ በሬውን እያሻሹ አዲሱ ዓመት ለህዝብ እና መንግስት የሰላም ዓመት የሚመኙበት መንገድ ነው። ልጆች ለወግ ለማዕረግ የሚበቁበት፣ መካኖች የሚወልዱበት፣ የተዘራው ለፍሬ የሚበቃበት ዓመት እንዲህን ፈጣሪያቸውን ይማፀናሉ።
በሦስተኛው ቀን የቱታው አባላትና የአካባቢ ሰዎች ተጠርተው በአባቶች ምርቃት ተደርጎ በአንድነት ሆነው ምክክር በማድረግ ለቀጣይ ዓመት የሚሆን እቅድ በማዘጋጀት ተጨዋውተው ይለያያሉ።
“በየቤቱ የሄደው ቅርጫ በፍጹም ለብቻ አይበላም” ያሉት አቶ እያሱ፤ በየአከባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞችን አፈላልጎ ማብላትና ማጠጣት በማከናወን በዓሉን በጋራ ያሳልፋሉ። ይህም በዓሉ አንዱ ለአንዱ ያለውን ወዳጅነትና አብሮነትን በማጠናከር ትስስርን የማጉላት አቅሙ ከፍተኛ ነው።
በሌላ በኩል ተጣልቶ የከረሙ ነዋሪዎች ከተገኙ በሰከነ መንፈስ በመነጋገር እርቀ ሰላም በማውረድ በንጹህ ህሊና፣ በአዲስ ምዕራፍ፣ በአዲስ ተስፋና በአዲስ መንፈስ አዲሱን ዓመት ይጀምራሉ።
ይህም “ባህሉ በዜጎች መካከል የሰላምና አብሮነት ምሰሶ መሆኑን ያመለክታል” ያሉት አቶ እያሱ፤ በንጹህ ልቦና በብርሃንና በተስፋ መጪውን ዘመን ለማሳለፍ እንዲቻል ጉልህ ሚና እንዳለው አጽንኦት ይሰጡታል።