መንግስት የግብርና ስራውን ለማዘመን የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው - ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የግብርና ስራውን ለማዘመን የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው - ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2017 (ኢዜአ)፦ መንግስት የግብርና ስራውን ለማዘመን የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
የግብርና ልማት ጣቢያ ባለሙያዎች የደረጃ ማሻሻያ ስልጠና የተመለከተ ውይይት በአዳማ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የግብርናና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የክልል ግብርና ቢሮ አመራሮችና የግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የግብርና ዘርፉን ለማሻገር በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግብርና ልማት ስራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድም የግብርና ጣቢያ ባለሙያዎች ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ስልጠናው ባለሙያዎቹ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያደርግና ላለፉት ዓመታት ሲያነሷቸው ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው ግብርናውን ለማዘመን በሰው ኃይል ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
ስልጠና በግብርናው ዘርፍ ያለውን መነቃቃት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚወስድና ለበርካቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ስልጠናው ለባለሙያዎቹ በስራ እድል ፈጠራ ልምድ እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የግብርና ጣቢያ ባለሙያዎች ስልጠና በግብርና ሚኒስቴርና በስራና ክህሎት ሚኒስቴር ትብብር በተመረጡ የግብርና ኮሌጆች እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።
ሁሉም የግብርና ልማት ጣቢያ ባለሙያዎች ከሶስት ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ስልጠናውን እንደሚወስዱ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።