ወጣቶችን በደንና ተፋሰስ ልማት በማሳተፍ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው--የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶችን በደንና ተፋሰስ ልማት በማሳተፍ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው--የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ
መቀሌ፤ መስከረም 11/2017 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የተፋሰስና የደን ልማትን ለማሳደግና የወጣቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን በጊዜያዊ አስተዳደሩ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሃብትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አለም ብርሃን ሃሪፈዮ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የተፈጥሮ ሃብትን በመንከባከብ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከልና ዘላቂ ልማት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።
በዚህም በክልሉ የተፋሰስና የደን ልማትን ለማሳደግና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
መንግስት ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ አለም ብርሃን፤ በክረምቱ በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተተከሉ ከ30 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተፋሰስና ተራራዎች ባሉበት አካባቢ ከ269 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በደን መልማቱን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፤ ይህንንም በ382 ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች የማሸጋገር ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል።
ይህም ወጣቶችና ሴቶችን በማደራጀት በንብ ማነብና በመስኖ ልማት በማሳተፍ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተጀመረውን ስራ ለማጠናከር እንዲቻል በቀጣይ ክረምት ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ ስራ ከወዲሁ የአፈር ዝግጅትና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን ለማከናወን 155 የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
ወጣት ሚኪኤለ ይሕደጎ በክልሉ ምስራቃዊ ዞን ጉለመኸዳ ወረዳ የመዛብር ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን፤ በአካባቢው የለማ ተፋሰስ ለወጣቶች የስራ እድልን እንደፈጠረላቸው ተናግሯል።
17 ወጣቶች ተደራጅተው ከ300 በላይ ቋሚ አትክልቶችና ፍራፍሬ ማልማት መጀመራቸው ገልፀዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናና በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸው ይታወሳል።