በኦሮሚያ ክልል ከመኸር አዝመራው የታቀደውን ምርት ለማግኘት የሰብል እንክብካቤ ስራው በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ከመኸር አዝመራው የታቀደውን ምርት ለማግኘት የሰብል እንክብካቤ ስራው በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ነው
አዳማ፤ መስከረም 11/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ከመኸር አዝመራው የታቀደውን ምርት ለማግኘት የሰብል እንክብካቤ ስራው በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ በመኸር እርሻ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ፣ በቦቆሎ፣ በገብስ፣ በሩዝና በተለያዩ ሰብሎች እየለማ መሆኑም ተመልክቷል።
በቢሮው የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ባለሙያ አቶ ሀብታሙ ንጉሳ እንደገለጹት፤ በመኸር አዝመራው ከለማው ሰብል 85 በመቶ በሚሆነው ላይ የሰብል እንክብካቤ እየተደረገ ነው።
የሰብል እንክብካቤውም የሰው ጉልበትን በተቀናጀ መልኩ በመጠቀምና ፀረ አረም ኬሚካሎችን ጥቅም ላይ በማዋል እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር ፀረ አረም፣ ፀረ ተባይና የሰብል በሽታ ኬሚካሎች ቀርበው እስከ አሁን 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሊትር ኬሚካል አገልግሎት ላይ መዋሉን ገልጸዋል።
አገልግሎት ላይ ከዋለው ኬሚካል ውስጥ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ፀረ አረም ኬሚካል ሲሆኑ 782 ሺህ ሊትር ፀረ ተባይ እንዲሁም 451 ሺህ ሊትር የሰብል በሽታ ኬሚካል ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ስንዴን ጨምሮ በዋና ዋና ሰብሎች ላይ የቢጫ ዋግ፣ የግንድና የቅጠል ዋግ፣ የስንዴ ራስ አድርቅ ተባዮች በሰብል ላይ የሚከሰትበት ወቅት በመሆኑ አርሶ አደሩ ጠዋት ማታ ማሳው ላይ ክትትል ማድረግና በሽታውን መከላከል እንዳለበት አመልክተዋል።
የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታ በሰብሉ ላይ ከታየ በሁለት ቀናት ውስጥ መድሀኒት ካልተረጨ ሰብሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ አርሶ አደሩና ባለሙያዎች በየዕለቱ ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በቢሮው የተክል ዳይሬክተር አቶ ቦና ሂርጳ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአረምና የሰብል በሽታ መከላከል ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰብል ተባይ ቁጥጥር ሳምንት በሚል መሪ ሀሳብ ከክልሉ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለሙያዎች ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ በስንዴ ምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውን የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታ ሰብሉ ከመዘርዘሩ በፊት መድኃኒት እንዲያገኝ ተገቢውን ክትትልና የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።