ዲጂታል መታወቂያን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋት ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2017(ኢዜአ)፦ ዲጂታል መታወቂያ በቀጣይ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋትና አገልግሎቱ የታለመለትን ሀገራዊ ግብ እንዲመታ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

በ2025 በሁሉም መስክ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ለሀገሪቱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እንዲሁም ለአሥር ዓመቱ ስትራቴጂክ የልማት ዕቅድ ስኬት ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው።

ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ አስቻይ ሁኔታን ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከፍተኛ አማካሪ ኦላና አበበ እንደሚሉት፣ ከወረቀት አሰራር ነጻና እርስ በእርሱ የተናበበ አገልግሎት ለመስጠት የዲጂታል መታወቂያ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።


 

በኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ዲጂታል የሆነ የመታወቂያ ሥርዓት እንዳልነበር ጠቅሰው ''ፋይዳ'' የተሰኘው መታወቂያ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።

በዚህ መታወቂያ አንድ ሰው አንድ ነው ያሉት ከፍተኛ አማካሪው መታወቂያውን ለመመዝገብ የባዮ-ሜትሪክና ዲሞግራፊክ መረጃ ይወሰዳል ብለዋል።

የግለሰቡ የአይንና የአስሩም የእጅ ጣቶች አሻራ እንዲሁም ፎቶግራፍ መረጃ ከተያዘ በሌላ ሰው ሥም በድጋሚ መመዝገብ የማይቻል መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ አቶ ኦላና ገለጻ፣ መታወቂያውን ለመውሰድ የተመዘገበ ግለሰብ በተሰጠው የመለያ ቁጥር የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላል።

ለዚህም የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር መግባባት በመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል።

ይሁንና በአንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው፣ በዲጂታል መታወቂያ ላይ ያለውን ብዥታ ለማጥራትና ወጥ ሥርዓት ለመዘርጋት በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮ-ቴሌኮም ከስተመር ኤክስፔሪያንስና ኳሊቲ ማኔጅመንት ክፍል ኃላፊ ሰለሞን አበራ ኢትዮ-ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አስቻይ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የዲጂታል መሰረተ ልማት ነው ብለዋል።


 

የዲጂታል መታወቂያ አንዱ መሰረተ ልማት መሆኑን ገልጸው በተለይም ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለማግኘትና አገልግሎቶችን ለማስተሳሰር የዲጂታል መታወቂያው ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ አገልግሎት በሙከራ ደረጃ ከተጀመረ ጥቂት የሚባሉ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን 10 ሚሊዮን ዜጎች መታወቂያውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን ታውቋል።

በቀጣይም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማስፋት ሁሉም ዜጋ መታወቂያውን እንዲያገኝ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል መታወቂያ በተለይም ማጭበርበርና ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ነው የጠቀሱት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የመታወቂያ ሥርዓት እንዲኖር ተቋማት በተናበበና በተቀናጀ መልኩ መስራት አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም