ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2017 (ኢዜአ)፦ በ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ወልቂጤ ከተማ ከመቻል ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።

መቻል በ2016 የውድድር ዓመት እስከ መጨረሻው ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ዋንጫውን ለማንሳት ሲፎካከር ቆይቶ በ63 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወቃል።

ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ አምና የመውረድ ስጋት ውስጥ የነበረ ክለብ ነው።

ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ በ23 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ከመውረድ መትረፉ አይዘነጋም።

ወልቂጤ ከተማና መቻል በ2016 የውድድር ዓመት በነበራቸው ግንኙነት መቻል ሁለቱንም ጨዋታዎች አሸንፏል።

በሌላኛው የአንደኛ ሳምንት መርሐ ግብር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከባህር ዳር ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር መመለሱ ይታወቃል።

ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በ2016 የውድድር ዓመት በ50 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም ትናንት በሊጉ በተደረጉ የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ አርባ ምንጭ ከተማን 2 ለ 1 እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና መቀሌ 70 እንደርታን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም