የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2024/25 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ክለብ ጋር ያከናውናል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ30 ዛንዚባር በሚገኘው አማኒ ኮምፕሌክስ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም በአበበ በቂላ ስታዲየም ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ 1 ለ 0 መሸነፉ ይታወቃል።
የ27 ዓመቱ ዚምባቡዌያዊው አጥቂ ፕሪንስ ምፑሜሌሎ ዱቤ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ተጫዋች ነው።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት ያንግ አፍሪካንስን ሁለትና ከዚያ በላይ ግቦችን አስቆጥሮ ማሸነፍ አለበት።
ንግድ ባንክ በመጀመሪያው ዙር የዩጋንዳውን ቪላ እንዲሁም ያንግ አፍሪካንስ የብሩንዲውን ቪታሎ ክለብን በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ለሁለተኛው ዙር ማለፋቸው ይታወቃል።
የ32 ዓመቱ ሞሪታኒያዊ አብደል አዚዝ ቦህ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ምክንያት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
ንግድ ባንክ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን የወከለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።
ክለቡ በ2016 ዓ.ም የውድድር ዓመት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል።