ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ የበይነ መንግስታት የትብብር ስምምነት ሊቀመንበር ሆና ተመረጠች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ የበይነ መንግስታት የትብብር ስምምነት(AFRA) ሊቀመንበር ሆና ተመርጣለች።

ከመስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም በኦስትሪያ ቪዬና ሲካሄድ የቆየው 68ኛው የዓለም የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ መጠናቀቁ ይታወቃል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጉባኤው ላይ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን የተለያዩ የጎንዮሽ ውይይቶችን አድርጓል።

ኢትዮጵያ ከጉባኤው ጎን ለጎን የአፍሪካ ኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ የበይነ መንግስታት የትብብር ስምምነት (AFRA) ሊቀመንበር ሆና ተመርጣለች።

ኢትዮጵያ ሊቀ መንበርነቷን ከአልጄሪያ የተረከበች ሲሆን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በሊቀ መንበርነት ተመርጠዋል።

የኢትዮጵያ የአፍራ ሊቀመንበርነት ከመስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ ለአንድ ዓመት ይቆያል።

በርክክቡ ላይ የዓለም የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ማሪያኖ ግሮሲ ተገኝተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ለስምምነቱ ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሊቀ መንበርነት ቆይታዋ በአፍሪካ እያደገና እየሰፋ የመጣውን የኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አላማ እንዲውል አበክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው በተለይም ለጤና፣ ለግብርና፣ ለማዕድን ልማት፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለኃይል ምንጭነት፣ለኢንዱስትሪና ሌሎች ዘርፎችን እንዲደግፍ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በሰኔ ወር 2016 35ኛውን የአፍራ የቴክኒክ ቡድን ስብስባ ማዘጋጀቷም ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በመረጃው አመላክቷል።

የአፍሪካ ኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ የበይነ መንግስታት የትብብር ስምምነትን የአቶሚክ ኤጀንሲው የአፍሪካ አባል አገራት የኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአህጉሪቷ የማህበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ያለውን ድርሻ ማሳደግና ማጠናከርን አላማ በማድረግ እ.አ.አ. በ1990 የፈረሙት ማዕቀፍ ነው።

ማዕቀፉ የኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ በጥናት፣ስልጠናና ልማት ማሳደግ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

ሁሉም የስሜት መግለጫዎች

93Muse Mele እና 92 ሌሎች

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም