የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዕድገት ለማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል - በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዕድገት ለማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል - በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት
አዲስ አበባ፤መስከረም 10/2017(ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው የኢትጵያን የኢንዱስትሪ ዕድገት ለማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ የተቀናጀ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ፕሮጀክት አስተባባሪ ኦልጅራ ኩማ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሬ ተመን፣ የገንዘብና ፋይናንስ ፖሊሲ፣ የመንግስት ገቢና ወጪ ፊስካል ፖሊሲን በማሻሻልና ዕዳን በማቃለል የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉ በገበያው እንዲመራ የሚያደርግ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጓ ይታወሳል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው በማዕድን፣ በሎጂስቲክስ፣ በቱሪዝም፣ በግብርና ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ላይ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ይነገራል።
ይህን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ የተቀናጀ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ፕሮጀክት አስተባባሪ ኦልጅራ ኩማ፤ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ለኢንዱስትሪ እድገት መሳለጥ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል ።
በተለይም የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በማነቃቃት የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያደርጉትን መዋዕለ ንዋይ ለማሳደግ ወሳኝ ዕድል ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ፈታኝ የነበሩትን የውጭ ምንዛሬ እና ከውጭ የሚገቡ የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን መፍትሔ ለመስጠትም ትልቅ አቅም እንደሆነ ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም በንግድና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችን የወጪ ንግድ አቅም በማጎልበት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያደርጉትን ድጋፍ የሚያሳደግ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪና የግብርናው ዘርፍ የሚያስመዘግበውን ፈጣን ዕድገትም ድርጅቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተለይም በኢንዱስትሪ ልማቱ ኢትዮጵያ በዘርፉ የተሻለ ዕድገት ካስመዘገቡ አገራት ልምድ በመውሰድ ልማት እንድታስመዘገብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የተረጋጋ፣ ጤናማ እና ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር ታስቦ የተተገበረ መሆኑ ይታወሳል።