ቀጥታ፡

የመንግስታቱ ድርጅት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤መስከረም 10/2017(ኢዜአ)፦የተባበሩት የመንግስታት ድርጅት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን በኢትዮጵያ የተመድ የልማት ፕሮግራም ዋና ተጠሪ ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር) ገለጹ።

25ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን "የሰላም ባህልን ማሳደግ'' በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተከብሯል።

በዝግጅቱም ላይ የሰላም ሚኒስቴር፣ የተባበሩት የመንግስታቱ ድርጅት፣ የሰብዓዊ መብትና የሰላም ግንባታ ተቋማት እንዲሁም የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዋና ተጠሪ ሳሙአል ዶ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በታሪክና ብዝኅነት የበለጸገችና ዘላቂ የሰላምና ደኅንነትን ለመፍጠር የምትተጋ ሀገር ናት ብለዋል።

በዚህም የህዝቦቿን አንድነትና የጋራ ብልጽግናን ለማስቀጠል የሰነቀችውን ራዕይ ፍትሕ፣ እኩልነትና ተስፋን የተጎናጸፈ የሰላም ባህል ለማዳበር የምታደርገውን ጥረት ተመድ ይደግፋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደትና የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ዘላቂ የሰላም ግንባታን በመፍጠር ዜጎች በመተማመን እንዲኖሩ ለማድረግ የማይተካ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

የሰለጠነ ውይይት ማድረግ ልዩነትን በመግባባት ለመቀየር ያስችላል ያሉት ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር)፤ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትም የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላምና በውይይት በመፍታት መተማመን ይፈጥራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን በመገንባት ልማቷን ለማስቀጠል በምታደርገው ጥረት የመንግስታቱ ድርጅት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የሴቶችና ወጣቶችን ሚና ማሳደግ የሚያስችሉ አጀንዳዎች ላይ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለዚህም ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሀገራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ዝግጅት ላይ በቅርበት እየሰሩ እንደሆነም አንስተዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ስራ አስፈፃሚ አወቀ አጥናፉ(ዶ/ር)፤ ሰላም በምንም አይነት ዋጋ ሊተመን የማይችል ከራስ የሚመነጭ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም ሁሉም ዜጋ የተሟላ ሀገራዊ ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ቀጣይነት ላለው የሰላም ግንባታ ሂደት በባለቤትነት መንፈስ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎችም ለሴቶችና ወጣቶች፤ በበጎ አድራጎትና ልዩ ልዩ የስልጠና ስራዎች ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለሴቶችና ወጣቶች የሚደረጉ የድጋፍ መርሃ ግብርም በመንግስት ፕሮጀክት ማዕቀፍ ስራ ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ዓለም አቀፉ ሰላም ቀን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት እ.አ.አ. በ1981 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት በየዓመቱ እንዲከበር ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም