ቀጥታ፡

የግብርና ናሙና ቆጠራ የምግብ  ዋስትናን ለማረጋገጥና ከተረጂነት ለመላቀቅ ለተያዘው ግብ መሳካት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተገለጸ

ጋምቤላ/ድሬዳዋ ፤መስከረም 10/2017 (ኢዜአ)፦ በአገሪቱ የግብርናውን ልማት በማዘመን የምግብ  ዋስትናን ለማረጋገጥና ከተረጂነት ለመላቀቅ ለተያዘው ግብ መሳካት የግብርና ናሙና ቆጠራ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተገለጸ።

በጋምቤላና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች  በአገር አቀፍ የግብርና ናሙና ቆጠራ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች ለ25 ቀናት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና  ዛሬ ተጠናቋል። 

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ  ፕሬዚዳንት  ዶክተር  ድሪባ ኢቲቻ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት በዘንድሮው  ዓመት የሚካሄደው  2ኛ ዙር አገር አቀፍ የግብርና ናሙና  ቆጠራ ለግብርናው  ትራንስፎርሜሽን  የጎላ ፋይዳ  ይኖረዋል ።

የግብርና ናሙና  ቆጠራው በተለይም ዘርፉን በማዘመን ምርታማነትን  በማሳደግ የምግብ  ዋስትናን  በማረጋገጥ  ከተረጂነት  ለመላቀቅ ለተያዘው ግብ እውን መሆን ትልቅ ግብዓት እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው  በንድፈ-ሃሳብና በተግባር የቀሰሙትን  እውቀት በመጠቀም  ጥራት ያለው መረጃ በመሰብሰብ ረገድ የተሰጣቸውን ኃላፊነት  በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ  አሳስበዋል ።

ሰልጣኞቹ በዩኒቨርስቲው  በነበራቸው ቆይታ ላሳዩት መልካም ስነ-ምግባር ምስጋና አቅርበዋል ።

በኢትዮጵያ  ስታትስቲክስ አገልግሎት የጋምቤላ  ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዱባለ ከበደ  በበኩላቸው የግብርና  ናሙና  ቆጠራው መንግስት በዘርፋ ለሚያወጣቸው  ፖሊሲዎችና የግብርና ልማት ስራዎች ትልቅ ግብዓትና አቅም  የሚፈጥር  መሆኑን ተናግረዋል ።

ሰልጣኞች  ወቅታዊና ጥራቱን የጠበቀ መረጃ በመሰብሰብ እንደ ሀገር ለታለመው ግብ እውን መሆን  የበኩላቸውን ድርሻ  እንዲወጡ  ጠይቀዋል ።

ሰልጣኞችም በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ለተጀመረው የግብርና ልማት ስራዎች  የሚያግዝ ጥራት ያለው መረጃ በመሰብሰብ  የዜግነት  ኃላፊነታቸውን  ለመወጣት  እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

ሰልጣኞቹ ከነሐሴ 16 ቀን 2016 ጀምሮ  በነበራቸው ቆይታ በንድፈ-ሃሳብና በተግባር  የተደገፈ ስልጠና  እንደተሰጣቸው  ተገልጿል ።

በተመሳሳይ በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ለመረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች ለ25 ቀናት ሲሰጥ የነበረው  ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

በስልጠናው ላይ ከሐረሪ ብሔራዊ ክልልና ከድሬዳዋ አስተዳደር የተመለመሉ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው 200 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።


 

ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራና ጥናት የሚሰማሩ ባለሙያዎች  የተጣለባቸው ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት በትክክል መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ግርማ እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ የሚካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራና  ጥናት በግብርናው ዘርፍ የተገኘውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ያግዛል ።

በተጨማሪም በትክክለኛና ተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረቱ አዳዲስ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ለመቀየስ ያለው ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች አገራዊ የግብርና ናሙና ቆጠራ ጥናት በአግባቡ እንዲያሳኩ  የንድፈ ሀሳብና የተግባር እንዲሁም  የቴክኖሎጂ ስልጠና ተሰቷቸዋል ብለዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን ዘሪሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው የግብርና ናሙና ጥናት ለግብርናው ዕድገት መሠረታዊ አስተዋፅኦ የሚያመጣ ወሳኝ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል ።

ጥናቱ በአገራችን እየተካሄዱ ከሚገኙ የሪፎርም ስራዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ታላቅ አላማ ዳር እንዲደርስ ሁላችንም ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም