በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ የዘመን መለወጫ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ተገቢ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ የዘመን መለወጫ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ተገቢ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል

ሶዶ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ የዘመን መለወጫና የአደባባይ በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ ተገቢ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በክልሉ በወላይታ ብሔር "ጊፋታ"፣ በጎፋ "ጋዜ መስቀላ"፣ በጋሞ "ዮ መስቀላ" እንዲሁም በኦይዳ "ዮኦ መስቀላ" የዘመን መለወጫ በዓላት ይከበራሉ።
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚከበሩትን እነዚህን የዘመን መለወጫ በዓላት በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሰሀ ጋረደው ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ መስቀልን ጨምሮ የሚከበሩ የዘመን መለወጫና የአደባባይ በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች "ጊፋታ፣ጋዜ መስቀላ፣ ዮ መስቀላ እና "ዮኦ መስቀላ" የዘመን መለወጫ በዓላት ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው እንደሚከበሩም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በመሆኑም በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ነው ያስታወቁት።
ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት በተከናወነ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በየአካባቢው ያሉ የጸጥታና የፖሊስ አባላት ስምሪት ወስደው ወደተግባር መግባታቸውንም ኮሚሽነር ፍሰሀ አመልክተዋል።
ለዚህም ፖሊስ፣ሚሊሻ፣የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከክልሉና ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከጸጥታ አካላት ጎን በመሆን ሰላምን የሚያስጠብቁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም የአካባቢያቸውን ሰላም እያስጠበቁ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የዘመን መለወጫ በዓላቱ በአደባባይ የሚከበሩ በመሆናቸው የትራፊክ ፍሰትን በመቆጣጠር አደጋንና ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው።
ሰላምን ማስጠበቅ የሁሉም ሀላፊነት መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ፍስሀ፣ የክልሉ ህዝብ በዓላቱ እሴታቸውን ጠብቀው በሰላምና በድምቀት እንዲከበሩ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።