ቀጥታ፡

አሰልጣኞች ውጤታማ አጥቂዎችና ግብ ጠባቂዎች ለማፍራት በዘመናዊ አሰለጣጠን ራሳቸውን ማብቃት ይኖርባቸዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2017(ኢዜአ)፦ አሰልጣኞች አጥቂዎችና ግብ ጠባቂዎች የማፍራት ኃላፊነታቸውን በሚገባ ለመወጣት ራሳቸውን በዘመናዊ ስልጠና እያበቁ መሄድ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና አሰልጣኝ በፀሎት ልዑል ሰገድ ገለጹ።

ለአንድ የእግር ኳስ ቡድን ግብ ጠባቂና አጥቂ እጅግ በጣም ወሳኝ ሲሆኑ፤ ግብ ጠባቂ በእግር ኳስ ጨዋታ ውጤት ይዞ ለመውጣት ከፍተኛ ሚና አለው።

ግብ ጠባቂ ከተከላካዮች የሚያልፈውን ኳስ በጥሩ ብቃት ካላዳነና አጥቂም እንዲሁ ከአማካዮች የሚላክለትን ኳስ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ጎል ማስቆጠር ካልቻለ አንድ ቡድን ስኬታማ አይሆንም።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባለፉት ዓመታት የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች እየጠፉ ክለቦች የውጪ ሀገር ተጨዋቾችን እያስፈረሙ እንደነበር ይታወሳል ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው የጨርሱት የውጪ ሀገር ተጨዋቾች እንደሆኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና አሰልጣኝ በፀሎት ልዑል ሰገድ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ ይህን ችግር ለመቅረፍ ለአሰልጣኞች ዘመኑን የዋጀ ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል ሲል ይናገራል።

በ2013 አቡበከር ናስር በኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ 29 ጎሎችን ካስቆጠረ በኋላ፤ በአንድ ዓመት 20 ጎሎችን የሚያገባ አጥቂ እየጠፋ ነው።

ይህ መሆኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ ለተፈጠረው ከፍተኛ ጎል የማስቆጠር ችግር አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል።

ዋና አሰልጣኙ እንደሚሉት፤ አጥቂዎችንም የሚያበቃው አሰልጣኙ በመሆኑ፤ አጥቂውን ብቻ ሳይሆን ለአጥቂው ጎል የሚሆኑ ኳሶችን የሚያቀብሉ አማካዮች ላይም መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

ያሉባቸውንም ድክመቶች ለይቶ በማስተካከል የማረምና ሥልጠናዎችን የመስጠት ሥራ ከአሰልጣኙ እንደሚጠበቅ ይናገራል።

አጥቂዎችም በበኩላቸው ከሚያገኙት ሥልጠና ባሻገር ራሳቸውን ለማብቃት መሥራትና የሌሎች አገሮች አጥቂዎችን ተሞክሮ መውሰድ እንደለባቸው ገልጸዋል።

ስለሆነም ግብ ጠባቂንና አጥቂን ትኩረት አድርገው ለሚያሰለጥኑ አሰልጣኖች፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ክለቦች በተከታታይ ዘመኑ የደረሰበትን ሥልጠና መስጠት እንዳለባቸው ተናግሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም