የአይነ ስውራንን ህልም ያለመለመ የብርሃን የአይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የአይነ ስውራንን ህልም ያለመለመ የብርሃን የአይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት
በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ የተገነባው የብርሃን የአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ባለፈው ዓመት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወቃል።
ትምህርት ቤቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ለማስተማር የተከፈተ ሲሆን፤ ምቹ የሆኑ የመማሪያ ክፍሎች፣ የመመገቢያ አዳራሾች ላይብረሪና ሌሎችም ዘመናዊ አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን የያዘ ነው።
ብርሃን የአይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2017 ዓ.ም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 312 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው።
ኢዜአ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ አይነስውራን ተማሪዎችን አነጋግሯል።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ ተወልዶ ያደገው ተማሪ ተስፋዬ ግርማ ትምህርቱን ተወልዶ ባደገበት አካባቢ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል መማሩን ይናገራል።
ትምህርቱንም ሲከታተል የመማሪያ ክፍሎች አለመመቸት፣ የግብዓትና የመሰረተ ልማት ችግር እንዲሁም በሌሎችም ጉዳዮች ሳቢያ ትምህርቱን በአግባቡ መከታታል ተስኖት እንደቆየ ይናገራል።
መንግስት በሰጠው ዕድል በብርሃን የአይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ መማር ከጀመረ ወዲህ እነዚያ ችግሮች ተቀርፈው የነገ ህልሙን እንዲያሰፋ እንደረዳው ተናግሯል።
የትምህርት ቤቱ ዘመናዊነትና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆኑን የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን በአግባቡ በመከታተልና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከአሁኑ በርትቶ እንዲሰራ ብርታት እንደሆነውም ጠቁሟል።
በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሃና አስማረ በበኩሏ ለትምህርቷ ካላት ጉጉትም ከሌላ አካባቢ አዲስ አበባ መጥታ ቤት በመከራየት ትምህርቷን ስትከታተል እንደቆየች ገልፃለች።
በብርሃን የአይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ያገኘችው ዕድል የቀደመ ችግሯን እንድትረሳ እንዳደረጋት ገልጻለች።
እንደ ብርሃን የአይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ሁሉ ሌሎችም በሀገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ ከማስቻል አንፃር ብዙ መሰራት አለባቸው ብላላች።
ከሀዋሳ ከተማ የመጣውና በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የ11ኛ ክፍል ትምህርት እየተከታታለ ያለው ተማሪ ቴዎድሮስ ሙሉጌታ በበኩሉ በተመቻቸ ሁኔታ ትምህርቴን እንድከታተል የረዳኝን ሁሉ አመሰግናለሁ ብሏል።
እሱም እንደሌሎቹ ተማሪዎች ትምህርቱን እንደልቡ ለመከታተል የትምህርት ቤት መሰረተ ልማቶችና ግብአት በበቂ ሁኔታ አለመደራጀቱ ፈተና ሆኖበት እንደቆየ ይገልፃል።
ነገር ግን አሁን ላይ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሰረተ ልማት እና የትምህርት ግብዓት ባለው ብርሃን አይነስውራን ትምህርት ቤት ገብቶ መማር በመቻሉ ደስተኛ መሆኑን ይናገራል።
ተማሪ ተስፋዬ በበኩሉ ትምህርት ቤቱ ዘመናዊ በመሆኑ እንደልባችን ተንቀሳቅሰን የተሻለ እውቀት እንድንገበይ እያደረገን ነው ብሏል።
ተማሪ ሀና አስማረና ተማሪ ቴዎድሮስ ሙሉጌታ፤ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ መከፈት ትምህርታቸውን ለመማር ምን ይጎድልብኛል የሚል ሀሳብ ሳይገባቸው ያለ ምንም ጫና በመማር ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ እያገዛቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የብርሀን አይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ኤፍሬም አይተንፍሱ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ በ2017 ዓ.ም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 312 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የመማር ማስተማር ሂደቱን ከመጀመሩ በፊት ለአይነስውራን ተማሪዎች የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች በማሟላት እርስ በእርስ ትውውቅ እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል።
ከተሰሩ ስራዎች መካከል ተማሪዎቹ ወደ ግቢው ሲገቡ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ ማድረግና የትምህርት ግብአቶችን አስቀድሞ ማዘጋጀት ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።
ተሻለ እውቀት እንዲኖራቸውን የማድረግ ስራ ትምህርት ቤቱ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
Like
Comment
Copy
Share