ኢትዮጵያ ከቬትናም ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ማስፋት ትፈልጋለች - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከቬትናም ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ማስፋት ትፈልጋለች - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ከቬትናም ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ማስፋት እንደምትፈልግ በኮሪያ ሪፐብሊክ እና በቬትናም የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ።
በቬትናም የሚገኙ የአፍሪካ አምባሳደሮች ስብስባ በመዲናዋ ሃኖይ ተካሄዷል።
በውይይቱ የቬትናም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ ሁንግ ቬት ተገኝተዋል።
በስብስባው የተሳተፉት በኮሪያ ሪፐብሊክ እና በቬትናም የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ የአፍሪካ ሀገራት ከቬትናም ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና አጋርነት ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከቬትናም ጋር ላላት ለረጅም ጊዜ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥና ይበልጥ ትብብሯን ለማጠናከር እንደምትሰራ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ግብርናና የአምራች ኢንዱስትሪን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ከቬትናም ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስፋትና ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግም ተናግረዋል።
አምባሳደር ደሴ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችና አማራጮች ላይ ገለጻ ማድረጋቸውን በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በቅርቡ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለቬትናም ፕሬዝዳንት ቶ ላም ማስገባታቸው የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያና ቬትናም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1976 መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።