ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኮደረስ ኢኒሸቲቭ ያዘጋጀውን የኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀታቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳቸው ሰልጣኞች ገለጹ

መቀሌ ፤ መስከረም 10/2017(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵየያ ኮደረስ ኢኒሸቲቭ ያዘጋጀውን የኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀታቸውን ከፍ በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚረዳቸው መሆኑን ሰልጣኞች ገለፁ።

በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ሰልጣኞች እንዳሉት፤ ስልጠናው በንግድም ይሁን በአገልግሎት ዘርፍ በመሰማራት ጥራትና ፍጥነት መሰረት ያደረጉ ሥራዎች ለመስራት ይረዳል።

የሲስተም ዲቨሎፐር ባለሙያ ወጣት ሙላይ በሪሁ እንደገለጸው፤ ሥልጠናው  በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት እውቀቱን ከፍ ለማድረግ አግዞታል።

አገራችን እየገባችበት ላለው በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ ለመስራት ስልጠናው በጣም ጠቃሚ መሆኑን የገለፀው ወጣት ሙላይ፤ "ማናቸውንም የንግድና የአገልግሎት ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለመስራት ስልጠናው  እውቀትን የሚያሰጨብጥ ነው" ብሏል።

ኤፍሬም መዓሾ የተባለው ሌላው ሰልጣኝ  እንዳለው በትምህርት ያገኘውን የኮምፒተር ሳይንስ እውቀት ይበልጥ ለማጎልበት እንዳገዘው አስረድቷል።

የፌዴራል መንግስት ለስልጠናውም ሆነ ለሰርተፊኬት የሚከፈለው ወጪ በመሸፈን ያዘጋጀውን ስልጠና ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምክረ ሀሳብ ለግሷል።

በግዚያዊ አስተዳደሩ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ቢሮ የእቅድና መረጃ ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ፀጋይ እንደሚሉት፤ የጥናትና ምርምር ስራዎችም ሆነ ሌሎች መረጃዎች ለመሰብሰብና ለመተንተን ስልጠናው መውሰድ ጠቃሚ ነው።  

ስልጠናው መሰጠት ከተጀመረ ከሁለት ወራት በላይ ማስቆጠሩን የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፤ ሆኖም በትግራይ ክልል ያለውን የስልጠና ፍላጎት ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የኮዲንግ ስልጠና መርሃ ግብር ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፤ ዘንድሮ ለትግራይ ክልል የተሰጠው እድል 53 ሺህ 597 ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አቶ ሰለሞን አስረድተዋል።

ስልጠናው በዋነኛነት ዳታ ሳይንስና አናሊስስ፣ ፕሮግራም ደቨሎፕመንትና  አንድሮይድ ደቨሎፕመንት የሚሉትን ያካተተ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ስልጠና በተጀመረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስልጠናው ከስራ ፈጠራ ባሻገር ለአገልግሎት ዘርፍ ኢንቨስትመንት መጎልበት ሚናው የጎላ መሆኑ ማመላከታቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም