ቀጥታ፡

የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የግብርና ቴክኖሎጂና የንግድ ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2017(ኢዜአ)፦ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የግብርና ቴክኖሎጂና የንግድ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አመራሮች ከቤጂንግ የንግድ ሙኒሲፓል ቢሮ የውጭ ኢኮኖሚና የንግድ ዘርፍ ዳይሬክተር ዡዋንግ ጂያንሮንግ ከተመራ የንግድ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸውም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ ተወካዮች ለልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ማዕቀፎች ገለጻ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ለቻይና ባለሀብቶች ተመራጭ የሆነች የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአገራቱን የሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ከቤጂንግ የንግድ ሙኒሲፓል ቢሮ በቅርበት እንደሚሰራ አስታውቋል።

የቤጂንግ የንግድ ሙኒሲፓል ቢሮ የውጭ ኢኮኖሚና የንግድ ዘርፍ ዳይሬክተር ዡዋንግ ጂያንሮንግ ኢትዮጵያ እምቅ የሆነ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት አመልክተዋል።

የቻይና ባለሀብቶች የግብርና የቴክኖሎጂና የንግድ ዘርፎችን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም