የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2017(ኢዜአ)፦ የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በድሬዳዋ ይጀመራል።
የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ በመቀሌ 70 እንደርታና ሀዲያ ሆሳዕና መካከል ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል።
ከምሽቱ 1 ሰዓት አርባ ምንጭ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።
መርሐ ግብሩ ነገ ቀጥሎ ሲውል ወልቂጤ ከተማ ከመቻል ከቀኑ 10 ሰዓት፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከባህር ዳር ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያሉ።
ኢትዮጵያ መድን የመጀመሪያ ሳምንት አራፊ ቡድን ነው።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካ ጋር ባለበት የመልስ ጨዋታ ምክንያት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሊያደርገው የነበረው የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን የሊጉ አክሲዮን ማህበር ገልጿል።
በ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19 ክለቦች ይወዳደራሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲና ስሑል ሽረ ዳግም ወደ ውድድር መመለሳቸው ይታወቃል።
አርባ ምንጭና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉ ክለቦች ናቸው።
በ2017 ዓ.ም የውድድር ዘመን በ19 ክለቦች መካከል ውድድር ተደርጎ 5 ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ እንደሚወርዱ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መግለጹ ይታወቃል።
በ2018 የውድድር ዓመት ሁለት ክለቦች ደግሞ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንደሚያድጉም እንዲሁ።
ይህንንም ተከትሎ በ2018 ዓ.ም ሊጉ ወደነበረበት የ16 ክለቦች የውድድር ፎርማት እንደሚመለስ ነው ማህበሩ ያስታወቀው።